ሪፖርት | አዳማ ሦስተኛ ድሉን ቡና ላይ አግኝቷል

አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ1 በመርታት ተከታታይ ድሉን አሳክቷል።

ሊጉ ከመቋረጡ በፊት አዳማ ከተማ ድሬዳዋን ሲረታ ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ ሲለያይ ከተጠቀሙት አሰላለፉ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የአራት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። አዳማ ከተማ ዊሊያም ሠለሞን ፣ ቻርለስ ሪቫኑ ፣ አህመድ ረሺድ እና አብዲሳ ጀማል ወጥተው መስዑድ መሐመድ ፣ አቡበከር ሻሚል ፣ ሱራፌል ዐወል እና አድናን ረሻድ ሲተኩ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በአንፃሩ ራምኬል ጀምስን በወንድሜነህ ደረጀ ፣ ዋሳዋ ጂኦፎሪን በኪያር መሐመድ ፣ አብዱልከሪም ወርቁን በአማኑኤል ዮሐንስ እና አማኑኤል አድማሱን በአንተነህ ተፈራ በመተካት ቀርበዋል።

ከፍ ባለ የማጥቃት ፍላጎት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአመዛኙ የኢትዮጵያ ቡና የበላይነት የታየበት ነበር። ኳስን ወደ መስመር ባጋደለ አጨዋወት የአዳማን ተከላካዮች ስህተት ለመጠቀም በጊዜ ጥረት ወደ ማድረጉ የገቡት ቡናማዎቹ 3ኛው ደቂቃ ላይ ጥራት ያላትን ቀዳሚ አጋጣሚ ፈጥረዋል። ጀሚል ወደ ኋላ ያቀበለውን ኳስ ሐቢብ መሐመድ ለመያዝ ሲዳዳ አንተነህ ተፈራ በብልጠት ነጥቆት ወደ ሳጥን ይዞ ከገባ በኋላ በቀላሉ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ሰይድ ሀብታሙ ይዞበታል። በይበልጥ ከመሐል ሜዳ ይልቅ የቀኝ ኮሪደሩን ለመጠቀም ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ሲያገኙ የአዳማ የመከላከል መዋቅር የሚሰራውን ስህተት በድግግሞሽ ለመጠቀም ሲጥሩ ተስተውሏል። በሌላ የቡድኑ ሙከራ ከቀኝ የተገኘን የቅጣት ምት ብሩክ ሲያሻማ ጫላ ጨርፎ የሰጠውን አንነተህ ተፈራ በአየር ላይ ኳሷን መቶ ሐቢብ መሐመድ ከጎሉ ስር በግንባር አውጥቶ ዳግም ስትመለስ ወንድሜነህ አግኝቶ ቢመታትም ተረባርበው ኳሷን አውጥተዋታል።

ከኢትዮጵያ ቡና የሚፈጠሩ የቅብብል ስህተቶችን ተጠቅሞ በፍጥነት ከራስ ሜዳ በመውጣት በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት አዳማዎች ቢሞክሩም የጨዋታ መንገዳቸው ግን እምብዛም ስኬታማ አልነበረም። 16ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ ከማዕዘን አሻምቶ ዮሴፍ የደረሰውን ወደ ግብ ሞክሮ ኳሷ ወጥታለች። ጎል ለማስቆጠር በትኩረት መንቀሳቀሳቸውን የቀጠሉት ቡናማዎቹ አማኑኤል እና ጫላ ባልተናበበ መልኩ ካመከኗት አጋጣሚ መልስ የመሪነት ግባቸውን ወደ ቋታቸው ከተዋል። 23ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ወደ ውስጥ ጫላ ተሺታ ያሻገረለትን ኳስ አንነተህ ተፈራ በግንባር ገጭቶ የመዲናይቱን ክለብ መሪ አድርጓል። ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ምላሽ ለመስጠት ብዙም ያልፈጀባቸው አዳማዎች ከቆመ ኳስ የአቻነት ጎልን አግኝተዋል ፣ መስዑድ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ጋናዊው ተከላካይ ሐቢብ መሐመድ በግንባሩ ገጭቶ ጨዋታውን 1ለ1 አድርጓል። ከአቻ ውጤቱ በኋላ ኢትዮጵያ ቡና በይበልጥ የአዳማን ተከላካይ ጫናን ውስጥ በሚከት እንቅስቃሴ ውስጥ በፍቃዱ አለማየሁ እና ጫላ ተሺታ አማካኝነት የሚያስቆጩ ዕድሎችን ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ አዳማዎች ቦና ዓሊ እና ቻርለስ ሊቫኑን ወደ ሜዳ በማስገባት የመሐል ሜዳ እና የአጥቂ ክፍሉ ላይ ማሻሻያ አድርገው ተመልሰዋል። ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በኳስ ቁጥጥሩ ሻል ብለው የታዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች 46ኛ ደቂቃ ላይ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለን ኳስ ጫላ ወደ ግብ ሲመታ ሰይድ ሀብታሙ ከግብነት ታድጓታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ቡናማዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ስተውታል። ፍቅሩ ጫላ ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘችውን ዕድል ብሩክ በየነ መቶ የግቡ የቀኝ ቋሚ ብረት መልሶበታል።

በፈጣን ሽግግር አልያም በሰንጣቂ ኳሶች ወደ ጨዋታ በመግባት ከየትኛውም የሜዳ ክፍል ጥቃትን መሰንዘር በሒደት የጀመሩት አዳማዎች ወደ መሪነት የመጡበትን ጎል ከመረብ አሳርፈዋል። 56ኛው ደቂቃ ላይ ከመልስ ውርወራ በፍጥነት ጀሚል ወደ ቀኝ የጣለለትን ኳስ ቢኒያም አይተን ወደ ሳጥኑ ገፋ አድርጎ ገብቶ ከጠባብ አንግል ኳሷን ከመረብ አዋህዷታል። ከግቧ በኋላ ዮሴፍ እና ቢኒያም አከታትለው ሁለት ተጨማሪ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ዕድሎችን ቢያገኙም ሊጠቀሙበት ግን አልቻሉም። መመራት ከጀመሩ በኋላ መስፍንን እና ዴሪክን አስገብተው የአጥቂ ቁጥራቸውን በማሳደግ የመጨረሻዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የግብ ዕድሎችን በመስፍን እና አንተነህ አማካኝነት ሲፈጥሩ ቢታይም በመጨረሻም ጨዋታው በአዳማ ከተማ የ2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮጵያ ቡናው ረዳት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በመጀመሪያው አርባ አምስት ብዙ ዕድል ፈጥረው አለመጠቀማቸውን የገለፁ ሲሆን መረጋጋት ባለመኖሩ ሊባክኑ እንደቻሉ እና ከዕረፍት መልስም መሐል ሜዳ ላይ መረጋጋቶች አለመኖራቸውን ተከትሎ ውጤት ስለ ማጣታቸው ተናግረዋል። የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ከዕረፍት በፊት ብዙ ኳስ ተሞክሮባቸው በተጋጣሚያቸው ስለ መበለጣቸው ካነሱ በኋላ ከዕረፍት መልስ ግን ተቆጣጥረው ጨዋታውን በመጫወታቸው የተሻሉ ሆነው ማሸነፍ መቻላቸውን ጠቁመዋል።