ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊጉን መምራት ጀምሯል

በሣምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ንግድ ባንኮች ኃይቆቹን 3ለ0 በመርታት በደረጃ ሠንጠረዡ አናት ላይ የተቀመጡበትን ድል አስመዝግበዋል።

በሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲገናኙ ኃይቆቹ በሮድዋ ደርቢ ሲዳማን 1-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ተባረክ ሔፋሞን አሳርፈው በአብዱልባሲጥ ከማል ሲተኩ ንግድ ባንኮች በአንጻሩ በአምስተኛው ሣምንት ወልቂጤ ከተማን 2-0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ዮናስ ለገሠ እና በረከት ግዛው በሀብታሙ ሸዋለም እና ሲሞን ፒተር ምትክ ገብተዋል።

12፡00 ሲል በተጀመረው ጨዋታ ገና ጨዋታው በተጀመረበት ቅፅበት በኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በኩል ብሩክ እንዳለ ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ሱሌይማን ሀሚድ ከሀዋሳ ተከላካዮች ሾልኮ ባደረጋት እና የግቡን ቋሚ ለትማ በተመለሰችው ሙከራ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ነበር።

ጨዋታው 20ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ንግድ ባንኮች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ኪቲካ ጅማ ተስፋዬ ታምራት ከእጅ ውርወራ ያቀበለውን ኳስ ከግራ መስመር ላይ ሆኖ ሲያሻግረው በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመግባት ኳሱን ያገኘው ዛሬ በቀኝ መስመር አጥቂነት የተሰለፈው ሱሌይማን ሀሚድ በድንቅ አጨራረስ በግንባሩ በመግጨት ግብ አድርጎታል።

ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በተሻለ መነቃቃት ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮችን ያደረጉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 32ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ኪቲካ ጅማ በቀኝ መስመር ከእጅ ውርወራ የተቀበለውን ኳስ እየገፋ በመውሰድ ወደ ውስጥ አሻግሮት አዲስ ግደይ ወደ ግብ ሲሞክረው ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉካጎ ቢመልስበትም ያንኑ ኳስ ያገኘው ሱሌይማን ሀሚድ መረቡ ላይ አሳርፎት ለራሱም ሆነ ለክለቡ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል።

ሀዋሳዎች ከወትሮው በተለየ በተዳከሙበት የመጀመሪያ አጋማሽ ብቸኛውን የጠራ የግብ ዕድል 34ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ሙጅብ ቃሲም ከቀኝ መስመር በተሻማ ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን አስወጥቶበታል።

በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት የአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ተጫዋቾች ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥም መሪነታቸውን ይበልጥ አጠናክረዋል። በረከት ግዛው በግራ መስመር ከተሰጠ የማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ያገኘው ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል በግንባሩ በመግጨት ግሩም ግብ አድርጎት ስሙን ከግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ አስጽፏል።

ከዕረፍት መልስ ሀዋሳዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር በተረጋጋ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም ግን 72ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ አቱላ ተቀይሮ በገባበት ቅፅበት በቀኝ መስመር ከተሰጠ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሚሊዮን ሰለሞን በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

ንግድ ባንኮች ጨዋታውን እንደጨረሱት በማመን ከነበራቸው ፈጣን እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዙ ሲሄዱ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መታተራቸውን የቀጠሉት ኃይቆቹ በአንጻሩ በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች በሙጅብ ቃሲም አማካኝነት ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። አጥቂው 75ኛው እኛ 78ኛው ደቂቃ ላይ ከመሃል በተሻገሩለት ኳሶች ባደረጋቸው ሙከራዎች የመጀመሪያው በግንባር የተገጨ ኳስ በግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ሲመለስበት በግራ እግር ያደረገውን ሁለተኛ ሙከራውን ደግሞ የግቡ የግራ ቋሚ አግዶበታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዋሳው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ያልጠበቁት ውጤት እንደሆነ በመግለጽ ያሰቡትን ታክቲክ የኢዮብ መውጣት እንዳፈረሰባቸው ሲናገሩ ሦስተኛው ግብም ይበልጥ ቡድናቸውን እንዳወረደው ጠቁመው የዳኞች ሰሞነኛ ስህተቶች ውጤት ቀያሪ እንደሆኑ እና ትኩረት ሊደረግባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በበኩላቸው ተጋጣሚያቸውን እንደጠበቁት ስለማግኘታቸው ጠቁመው በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠሯቸው ግቦች ጨዋታውን ለመቆጣጠር እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።