የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የ3ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ዛሬ አራት ጨዋታዎች አስተናግዶ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዕለቱን ሰፊ ውጤት አስመዝግቧል።

ረፋድ አራት ሰዓት ላይ የአዲስ አበባን ቡድኖች ያገናኘው መርሐግብር በመቻል አሸናፊነት ሲጠናቀቅ የመቻል የተከላካይ መስመር ጠንካራ ሆኖ መውጣት የቻለበትን ቀን አሳልፏል። መጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ብልጫ የወሰዱት ልደታዎች ጨዋታውን ተቆጣጥሮ መጫዎት የቻሉ ሲሆን የግብ ዕድል ማግኘት ግን ተስኗቸዋል። መቻል በበኩሉ በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ክልል መሄድ ቢችልም በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተው 0-0 በሆነ ውጤት ወደመልበሻ ክፍል ገብተዋል።

መቻሎች በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን ተቆጣጠረው ለመጫወት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው በ55ኛው ደቂቃ መሰረት ወርቅነህ ያገኘችውን አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ግብነት ቀይራ እንዲያሸንፉ ያደረገች ሲሆን ልደታዎች በበኩላቸው የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ሊሳካላቸው አልቻለም።

ቀን 8:00 ሰዓት ላይ በንግድ ባንክ እና አዲስአበባ ከተማ መካከል በተደረገው ጨዋታ ንግድ ባንክ 3ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃቸውን ካሉበት ከፍ ማድረግ ችለዋል። የንግድ ባንክ የማሸነፊያ ግቦችን ሎዛ አበራ እና ብርቄ አማረ ያስቆጠሩ ሲሆን ሎዛ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችላለች።

ተመጣጣኝ ጨዋታ በሚመስለው በ8:00 ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች እኩል በሚባል ደረጃ እስከ 30ኛው ደቂቃ ድረስ ኳስን ተቆጣጥረው የተጫወቱ ሲሆን ሎዛ አበራ የመጀመሪያውን ግብ በማስቆጠር ንግድ ባንክን መሪ ካደረገች በኋላ በአዲስአበባ በኩል ትንሽ የመቀዛቀዝ ስሜት ይታይ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽም በሎዛ አበራ ብቸኛ ግብ የተጠናቀቀ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ንግድ ባንኮች ሙሉ የጨዋታ በላይነት በመውሰድ በ62ኛው ደቂቃ ብርቄ አማረ ከመሃል ሜዳ አከባቢ አክርራ መትታ ባስቆጠረችው ግቢ መሪነታቸውን 2-0 ማድረግ ችለዋል።

አዲስ አበባ ከተማ በአንፃሩ በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎቸን ቢያደርጉም ሁለተኛ ግብ ሲቆጠርባቸው ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ኳስን ወደ ግብነት መቀየር ተስኗቸዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ አልቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ሎዛ አበራ ከግብ ክልል መግቢያ አከባቢ በአንድ ለአንድ ቅብብሎሽ ኳስን ወደ ግብነት በመቀየር ንግድ ባንኮች 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፈው እንዲወጡ አድርጋለች።

10:00 ሰዓት በተመሳሳይ ሰዓት በተለያዩ ሜዳዎች በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል። 

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሀዋሳ ከተማ እና በአዳማ ከተማ መካከል በተደረገ ጨዋታ አዳማ 1-0 በሆነ ውጤት ያሸነፈ ሲሆን የመጀመሪያ አጋማሽ ያለግብ ተጠናቆ በሁለተኛ አጋማሽ በ62ኛው ደቂቃ ላይ በሄለን እሸቱ አማካኝነት ባስቆጠሩት ግቢ አዳማ ከተማዎች አሸናፊ መሆን ችለዋል። ሳቢ በነበረው በዚህ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች የመጀመሪያ አጋማሽ ትንሽ ተቀዛቅዘው የገቡ ሲሆን አዳማ ከተማ በአንፃሩ ኳስን ተቆጣጥሮ ቢጫወትም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተው 0-0 በሆነ ውጤት ወደ ዕረፍት ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ መነቃቃት በታየበት በዚህ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች የሊጉ መሪነታቸውን ለማስቀጠል ትልቅ ትግል ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን አዳማ ከነማዎች በ62ኛው ደቂቃ ሄለን እሸቱ ከመስመር የተሻገረላትን ኳስ ከመረብ በማገናኘቷ አሸናፊ መሆን ችለዋል። ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው እስከመጨረሻው ደቂቃ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ያደረጉት ጥረት ሳይሰምር ለሽንፈት ተዳርገዋል። በተመሳሳይ ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲዳማ ቡናን በገጠመበት ጨዋታ ባዩሽ ኪምባ በራሷ ላይ ባስቆጠረችው ግብ 1-0 መርታት ችሏል።

የሊጉ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከመጪው ዓርብ እና ቅዳሜ እንደሚከናወኑ ይጠበቃል።