የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ6ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በመንተራስ ተከታዩን የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሰርተናል።

አሰላለፍ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

መክብብ ደገፉ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡናዎች ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለ ግብ በተለያዩበት ጨዋታ ላገኙት አንድ ነጥብ የግብ ጠባቂያቸው መክብብ ደገፉ አስተዋጽኦ የጎላ ነበር። ግብ ጠባቂው በተለይም በሦስት አጋጣሚያዎች ያዳናቸው ፈታኝ የሆኑ የግብ ሙከራዎች በቦታው ተመራጭ አድርገውታል።

ተከላካዮች

ፍራኦል መንግሥቱ – ባህር ዳር ከተማ

የጣና ሞገዶቹ ፈረሠኞቹ ላይ የ2-1 ድል ሲቀዳጁ የመስመር ተከላካዩ ፍራኦል የተሳካ ቀን ማሳለፍ ችሏል። ክለቡ መሪ የሆነበትን የመጀመሪያ ግብ በደካማ እግሩ በጥሩ አጨራረስ ማስቆጠር ሲችል ከግቡ ባሻገርም ከፍ ባለ የማጥቃት ተሳትፎ ያደረገው እንቅስቃሴ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ እንዲመረጥ ምክንያት ሆኗል።

ፈቱዲን ጀማል – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የኋላ መስመራችንን ካዋቀርንባቸው ተጫዋቾች አንዱ ፈቱዲን ይገኝበታል። የባንክ አምበል ቡድኑን በምሳሌ ከመምራቱ ባለፈ አዲስ የነበረውን የኋላ መስመር መዋቅር ሲመራ የነበረበት መንገድ ድንቅ ነበር። እርግጥ ቡድኑ ከተጋጣሚው ያን ያህል ጫና ባይበረክትበትም የቡድኑን የኋላ መስመር በሚገባ አስከብሯል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከመዓዘን ምትም የቡድኑን ሦስተኛ ግብ በግንባር አስቆጥሯል።

አማኑኤል ተርፉ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ሲያስተናግድ የመሃል ተከላካዩ አማኑኤል ተርፉ ብቃት ግን አስደናቂ ነበር። አማኑኤል በተሻለ የራስ መተማመን በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ብልጫን በመውሰድ ለክለቡ የኋላ ደጀን በመሆን የራሱን ኃላፊነት በስኬት ያጠናቀቀ ሲሆን ምንም እንኳ ከማስተዛዘኛነት ባያልፍም የቡድኑን ብቸኛ ግብም በግንባር በመግጨት ማስቆጠር ችሏል።

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ድሬዳዋ ከተማ

የቀኝ መስመር ተከላካዮች ጎልተው ባልታዩበት የጨዋታ ሣምንት አሰጋኸኝ በአንጻራዊነት የተሻለ ነበር። ተጫዋቹ በሁለት አጋጣሚዎች ከቡድኑ የግብ አፋፍ ያስወጣቸው ኳሶችም ቡድኑ ላገኘው አንድ ነጥብ አስተዋጽኦ ነበራቸው። ሆኖም በማጥቃቱ ረገድ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ አድርጎ ባንመለከተውም ከላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች በቦታው ተመራጭ ሆኗል።

አማካዮች

ጋቶች ፓኖም – ፋሲል ከነማ

ፋሲል ከነማ በሳምንቱ ብዙም ሳይፈተን አስተማማኝ ድል ሲያገኝ በአማካይ መስመሩ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጋቶች ነው። የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ረገድ የተዋጣለት ጋቶች በተለይ አብዛኛውን ደቂቃ በላይኛው ሜዳ በማሳለፍ እድገት ያላቸው የፊትዮሽ እና የጎንዮሽ ኳሶችን በማቀበል የቡድኑ የጥቃት መነሻ አማራጭ ሲሆን አስተውለናል።

ኤርሚያስ ሹምበዛ- ኢትዮጵያ ቡና

ምንም እንኳን ቡድኑ በጨዋታው ማሸነፍ ባይችልም ወጣቱ አማካይ ቡድኑ በአዳማው ጨዋታ በተለይ ከኳስ ውጭ ከፍ ባለ ጫና በመጫወት በሜዳው የላይኛው ክፍል ኳሶችን በመንጠቅ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደርግ በነበረው ጥረት ውስጥ ቁልፉ ሰው ነበር። በተለይ እሱ በነበረበት የኢትዮጵያ ቡና የግራ ወገን በኩል የነበሩትን የአዳማ ተጫዋቾች በከፍተኛ ትጋት ኳስ ለመማስጣል ያደርግ የነበረው ጥረት አስደናቂ ነበር።

ዓባይነህ ፌኖ – ባህርዳር ከተማ

የፍሬው ሰለሞንን መጎዳት ተከትሎ የመጫወት ዕድል በማግኘት የብዙዎቹን ትኩረት የሳበው ዓባይነህ ባህር ዳር ከተማዎች ፈረሠኞቹን 2-1 በረቱበት ጨዋታ ላይም ካደረገው ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ባሻገር ለሁለቱም ግቦች አመቻችቶ ማቀበል መቻሉ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ አድርገውታል።



አጥቂዎች

አቤል ነጋሽ – መቻል

መቻሎች ኢትዮጵያ መድንን 1-0 ሲያሸንፉ የመስመር አጥቂው የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነበር። አቤል የክለቡን ብቸኛ የማሸነፊያ ግብ ከሳጥን ውጪ ማስቆጠር ሲችል ያደረገው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎችም የመስመር አጥቂዎች ጎልተው ባልታዩበት የጨዋታ ሣምንት የተሻለ ተመራጭ አድርገውታል።

ሱለይማን ሀሚድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ንግድ ባንኮች ሀዋሳን 3-0 በመርታት የሊጉ መሪ ሲሆኑ የመጫወቻ ቦታ በመቀየር በመስመር አጥቂነት ቦታ ላይ የተሰለፈው ሱሌይማን ሁለት ግቦችን በስሙ ማስመዝገብ ችሏል። ተጫዋቹ በተለይም ቡድኑን መሪ ያደረገችዋን ግብ ያስቆጠረበት መንገድ አድናቆት ያስተረፈለት ሲሆን ያደረገው ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴም በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ አድርጎታል።

ጌታነህ ከበደ – ፋሲል ከነማ

የዐፄዎቹ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ጌታነህ ከበደ ክለቡ ሀምበሪቾን 3-0 ሲረታ ለቡድኑ አንድ ግብ በማስቆጠር የነበረበትን የግብ ርሃብ በመጠኑ ማስታገስ ሲችል ምኞት ደበበ ላስቆጠረው ግብም አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። አጥቂው ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባደረገው አስተዋጽኦ በቦታው እንዲመረጥ ምክንያት ሆኗል።

አሰልጣኝ – በጸሎት ልዑልሰገድ

ከስድስት ጨዋታዎች አራቱን አሸንፎ በሁለቱ አቻ በመለያየት በ14 ነጥብ የሊጉ መሪ የሆኑት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሚጫወተው ቡድናቸው የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። አሰልጣኙ ባሳለፍነው የጨዋታ ሣምንትም ንግድ ባንክ ሀዋሳ ከተማ ላይ 3-0 ድል ሲቀዳጅ ሱሌይማን ሀሚድ ላይ ያደረጉት የቦታ ቅያሪ እጅግ ውጤታማ ያደረጋቸው ሲሆን ለሀዋሳ አጥቂዎችም ክፍት ቦታዎችን በማሳጣት ባደረጉት የተደራጀ እንቅስቃሴ የ 6ኛ ሣምንት ምርጥ ቡድናችንን እንዲመሩ ሆኗል።

ተጠባባቂዎች

ሰዒድ ሀብታሙ – አዳማ ከተማ
ፍሬዘር ካሳ – ባህር ዳር ከተማ
አስቻለው ታመነ – መቻል
ባሲሩ ኦማር – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ጋዲሳ መብራቴ – ወልቂጤ ከተማ
ኪቲካ ጅማ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
አንተነህ ተፈራ – ኢትዮጵያ ቡና