የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የ3ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች ሲካሄዱ ሀምበሪቾ ፣ ቦሌ ክ/ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።

ረፋድ አራት ሰዓት ላይ መደረግ የጀመረው የሀምበሪቾ  እና የጊዮርጊስ ጨዋታ በሀምበሪቾ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ሀምበሪቾ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ተሽለው የታዩት ሀምበሪቾዎች ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ጫና ፈጥረው መጫዎት ችለው ነበር። በተደጋጋሚ የተቃራኒ ግቢ ክልል ኳስን ገፍተው ይዞ ሲገቡም ተስተውለዋል። በዚህም በ23ኛው ደቂቃ ላይ የጊዮርጊስ ተከላካዮች የሰሩትን ክፍተት ተጠቅማ ፍሬነሽ ዩሐንስ ሀምበሪቾን ቀዳሚ አድርጋለች። ኳሶችን ተቆጣጥረው ሲጫወቱ የነበሩት ሀምበሪቾዎች በ36ኛው ደቂቃ ሄለን መንግሥቱ ከመሃል ሜዳ አከባቢ አክርራ በመምታት ባስቆጠረችው ግቢ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ በማድረግ ዕረፍት ወጥተዋል።

በሁለኛው አጋማሽ ተሻሽሎ በመመለስ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው  የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ሁለተኛ አጋማሽ እንደተጀመረ በ46ኛው ደቂቃ በምህረቱ ቱንጆ አማካኝነት ግቢ በማስቆጠር ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሞከረ ቢሆንም ተጨማሪ ግቢ ማስቆጠር ባለመቻሉ ጨዋታው 2-1 በሆነ ውጤት በሀምበሪቾ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከሰዓት 08:00 ጅማረውን ያደረገው የድሬዳዋ ከተማ እና የቦሌ ክ/ከተማ ጨዋታ በቦሌ 1ለ0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ በመጀመሪያው አጋማሽ በ18ኛው ደቂቃ የቦሌዋ ጤናዬ ሌታሞ ከመስመር የተሻገረላትን ኳስ የድሬዳዋ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾችን አዘናግታ በማግባት ቡድኗ እንዲያሸንፍ ማድረግ ችላለች። ግቢ ከተቆጠረባቸው ደቂቃ አንስተው የአቻነት ግቢ በተደጋጋሚ ሲሞክሩ የተስታዋሉት የድሬዳዋ ቡድን አባላት የቦሌን የተከላካይ መስመር ጥሶ ገብተው ግቢ ማስቆጠር ተስኗቸው 1-0 እየተመሩ እረፍት ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉ ቢሆንም ጥሩ ሆኖ የዋለው የቦሌ የተከላካይ መስመር ወደ ኋላ በማፈግፈግ ወጤታቸውን ለማስጠበቅ ሲጥሩ የተመለከትን ሲሆን ጎላቸውን ሳይስደፍሩ ውጤቱን አስጠብቀው 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

የመጀመሪያ ቀን የመጨረሻ ጨዋታ በሆነው ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ይርጋጨፌ ቡና ላይ ሦስት ግብ በማስቆጠር 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ፍፁም የጨዋታ ብልጫ ወስዶ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የአርባምንጭ ከተማ ቡድን በ24ኛው ደቂቃ በእርስ በርስ ቅብብሎሽ የይርጋጨፌ ቡናን ግቢ ክልል በመድረስ በፎዚያ መሐመድ አማካኝነት ቀዳሚ በመሆን ዕረፍት መውጣት ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም ይበልጥ ኳስን ወደፊት ገፍተው ሲጫዎቱ የተስተዋሉት አርባምንጭ ከተማዎች በሰርካለም ባሳ ላይ የግቢ ክልል አከባቢ በተሰማራባቸው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት በማግኘት ራሷ ሰርካለም በመምታት መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሳድገዋል። በ84ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ሰርካለም ባሳ አየር ላይ እያለ መትታ ባስቆጠረቺው በሦስተኛው ድንቅ ግብ አርባምንጭ ከተማዎች 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። በዚህም በሰባት ነጥቦች ቢያንስ እስከነገ ጨዋታዎች ድረስ ሊጉን መምራት ጀምረዋል።

የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው ሲካሄዱ 04:00 ላይ ልደታ ክ/ከ ከ መቻል ፣ 08:00 ላይ አዲስ አበባ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም 10:00 ላይ አዳማ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ሲገናኙ በተመሳሳይ 10:00 ላይ የሲዳማ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሩክ ጨዋታ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እንደሚከናወን ይጠበቃል።