የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ቅጣቶችን አስተላልፏል

የስድስተኛ ሳምንት መርሐግብርን በመንተራስ አራት ተጫዋቾች እና ሦስት ክለቦች ጠንከር ያሉ ቅጣቶችን አስተናግደዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ የሰሞኑ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት መርምሮ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ይፋ አድርጓል።

ከተላለፉት ቅጣቶች መካከል በቀጥታ የታዩ ቀይ ካርዶችን ተከትሎ አራት ተጫዋቾች ላይ የተላለፉ ቅጣቶች ተካተዋል። አክሲዮን ማህበሩ ተጫዋቾቹን ለቀጥታ ቀይ ካርድ የዳረጉትን ጥፋቶች በመጥቀስ እና በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ አንቀፆችን በመጥቀስ ውሳኔዎችን ሲሰጥ የሀምበሪቾው ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ የተጋጣሚን ቡድን ግልፅ ግብ ዕድል በማበላሸቱ ሦስት ጨዋታ እንዲታገድ ፣ የወልቂጤ ከተማው ተስፋዬ መላኩ የተጋጣሚን ተጫዋች በመማታቱ አራት ጨዋታ እንዲታገድ ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሞሰስ ኦዶ በተመሳሳይ የተጋጣሚን ተጫዋች በመማታቱ አራት ጨዋታ እንዲታገድ ፣ የመቻሉ ግሩም ሀጎስ የተጋጣሚን ቡድን ግልፅ ግብ የማግባት ዕድል በማበላሸቱ ሦስት ጨዋታ እንዲታገድ ሲወስን በእያንዳዱ ተጫዋች ላይ የሦስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትም ጥሏል።

ከተጨዋቾች በተጨማሪ ክለቦችን ባገኘው ቅጣት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የዕለቱ ዳኞችን አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸውና የውሀ መጠጫ ፕላስቲክ ጠርሙስ ወደ ሜዳ በመወርወራቸው ሀምሳ ሺህ ብር እንዲሁም ቁሳቁስ ወደ ሜዳ በመወርወራቸው ሀያ አምስት ሺህ ብር በድምሩ ክለቡ ሰባ አምስት ሺህ ብር እንዲከፍል ተወስኗል።

አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች የዕለቱ ዳኞችን አፀያፊ ስደብ በመሳደባቸው እና ከዚህ በፊት አፀያፊ ስደብ በመሳደብ ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው ክለቡ ሰባ አምስት ሺህ ብር እንዲከፍል ተወስኗል። በዚሁ ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም የራሳቸውን ቡድን ተጫዋቾች እና የቡድን አመራሮች አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ለመደባደብ እና የኃይል ጥቃት ለማድረስ ስለመሞከራቸው ሪፖርት የቀረበ ሲሆን የክለቡ ደጋፊዎች በተደጋጋሚ ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው ክለቡ አንድ መቶ ሺህ ብር እንዲከፍል ተወስኗል።

በተጨማሪም መቻል ፣ አዳማ ከተማ ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾቻቸው በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ እያንዳዳቸው አምስት ሺህ ብር እንዲከፍሉ ተወስኗል።