አዳማ ከተማ ተጫዋቾቹ ላይ የዲሲፒሊን ውሳኔ አስተላለፈ

በተደጋጋሚ የዲሲፕሊን ጥሰት በፈፀሙ ሁለት ተጫዋቾች ላይ አዳማ ከተማ የቅጣት ውሳኔ ወስኗል

በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ እየተመሩ በ2016 የውድድር ዓመት ምንም ሽንፈት ሳያስተናግዱ ጥሩ የውድድር ጅማሮ እያደረጉ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች ሁለት ተጫዋቾቻቸው ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ መውሰዳቸው ታውቋል። ቅጣት የተላለፈባቸው ተጫዋቾች ዊልያም ሰለሞን እና አብዲሳ ጀማል ሲሆኑ እነዚህ ተጫዋቾች በሆቴላቸው ውስጥ እና ከሆቴል ውጪ ከተጫዋቾች ሥነ ምግባር ባፈነገጠ ሁኔታ ያልተገባ ድርጊት ሲፈፅሙ በማስረጃ በመያዙ ላጠፉት ጥፋት የዲሲፕሊን ቅጣት የተላለፈባቸው መሆኑ ታውቋል። በዚህም መሰረት የገንዘብ ቅጣት ሲጣልባቸው ላልተወሰነ ጊዜ ያህል ወደ ተስፋ ቡድኑ ወርደው እንዲሰሩ ክለቡ ከውሳኔ ላይ ደርሷል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ተጫዋቾች ተመሳሳይ ጥፋት ፈፅመው ውሳኔ ተላልፎባቸው እንደነበረ እና ይቅርታ በመጠየቃቸው ወደ ቡድኑ እንዲመለሱ ቢደረግም ከጥፋታቸው ሊታረሙ ባለመቻላቸው በቀጣይ እንደ አስፈላጊነቱ ከበድ ያለ ቅጣት ሊወሰንባቸው እንደሚችል ከክለቡ ሰምተናል።