የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኞች ያስገቡት መልቀቂያ ተቀባይነት አግኝቷል

ኢትዮጵያ ቡናን ያለፉትን የስምንት ሳምንት ጨዋታ የመሩት ሁለቱ የውጭ ሀገር አሰልጣኞች ያስገቡት መልቀቂያ ተቀባይበት አግኝቷል።

የ2016 የውድድር ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ስራ አመራር ቦርድ በሀገር ውስጥ አሰልጣኝ እምነት በማጣት ቡድኑ በውጭ ሀገር አሰልጣኞች እንዲመራ በመወሰን ዋና እና ምክትል አሰልጣኞች ከውጭ ሀገር ማስመጣቱ ይታወቃል።

በዋና አሰልጣኝነት ሰርቢያዊው ኒኮላ ካቫዞቪች በአካል ብቃት አሰልጣኝነት ሰርቢያዊው ማርኮ ቭላስቪች ሲሆኑ እነዚህ አሰልጣኞች ያለፉትን አምስት ወራት ቡድኑን ለቅድመ ውድድር ከማዘጋጀት አንስቶ በሊጉ የስምንት ሳምንት ጉዞ ማደረጋቸውም ይታወሳል። ዛሬ የክለቡ ይፋዊ የራድዩ ፕሮግራም እንዳሳወቀው ከሆነ ሁለቱም አሰልጣኞች የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን እና የክለቡም ስራ አመራር ቦርድ ያቀረቡትን ጥያቄን መቀበሉን እና ሁለቱም ከክለቡ ጋር መለያየታቸውን አሳውቋል።

በምትካቸውም ምክትል አሰልጣኙ ነፃነት ከነገው የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ጀምሮ ቡድኑን እንዲመሩ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው አያይዘው ገልፀዋል። ሁለቱ የውጭ ሀገር አሰልጣኞች ያስገቡት መልቀቂያ በምን ምክንያት እንደሆነ እና ቦርዱም ሀሳባቸውን ስለተቀበለበት ምክንያት ዝርዝር መግለጫ አልሰጠም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቡድን መሪው ባገኘው መረጃ መሰረት ደግሞ አሰልጣኙ በአሁኑ ሰዓት በልምምድ ሜዳ ላይ እያሰለጠኑ መሆናቸውን አውቀናል።

ሶከር ኢትዮጵያ ሁለቱ አካላት ለመለያየት ያበቃቸውን ዝርዝር ጉዳይ ተከታትላ ወደ እናንተ የምታደርስ ይሆናል።