ከነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ በፊት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ሀሳባቸውን አጋርተውናል

👉 “በዚህ ጨዋታ ላይ ውጤታማ ሆነን ደጋፊዎቻችንን መካስ እንፈልጋለን።”

👉  “ያለንበት ደረጃ ኢትዮጵያ ቡናን የሚመጥን አይደለም።”

👉 “እነርሱ ይዘውት ከሚመጡት በላይ እኛ የምንቀርብበት የጨዋታ መንገድ ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ።”

የሸገር ደርቢ በኢትዮጵያ ቡና እና በቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል ተጠባቂው ጨዋታ ይደረጋል። ከጨዋታው በፊት በሁለቱ ቡድን ዝግጅት ለጨዋታው ስለሰጡት ትኩረት እና ነገ ስለሚጠብቁት ውጤት አስመልክቶ አስቀድመን ከአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጋር ያደረግነውን ቆይታ አስነብበናችሁ ነበር። በማስከተል የኢትዮጵያ ቡና ጊዜያዊ አሰልጣኝ ከሆኑት ነፃነት ክብሬ ጋር ያደረግነውን ቃለ መጠይቅ እንዲህ አሰናድተን አቅርበነዋል።

ለደርቢው ምን ያህል ተዘጋጅታችኋል…?

“የራሳችን ትንሽ ጫናዎች አሉብን። ይሄን ነገር መቀየር እንፈልጋለን። እኔ ከጀመርኩ በኋላ ከተጫዋቾቹ ጋር ውይይት አድርገናል ፤ ይሄንን ጨዋታ መነሻ ማድረግ አለብን። ለደርቢ ጨዋታዎች የተለየ ዝግጅት አታደርግም ነገር ግን የተለያዩ ስሜቶች ሊኖሩህ ይገባል። የተለየ ተነሳሽነት ፣ አልሸነፍ ባይነት ፣ በእያንዳንዱ ግንኙነቶች አሸናፊ መሆን አለብህ ፣ እንደ ቡድን በጋራ መጫወት አለብህ ስለዚህ ደርቢ በራሱ ልዩነት የሚፈጥረው እንደነዚህ ዓይነት ስሜቶች ይፈልጋል እና በስነልቦናም በሚገባ እየተዘጋጀን ነው። እንደ ሌላው ጊዜ መዘጋጀት ባለብን ልክ እየተዘጋጀን ነው። ነገር ግን ይሄንን ጨዋታ ለቀጣይ ጨዋታዎቻችን እንደ ጥሩ መነሳሻ እንዲሆነን ልጆቻችን ላይ ስራ ሠርተናል።”

ከተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ ስለማግኝታቸው እና ስለ ደርቢው ጨዋታ ዋጋ ከፍ ማለት…?

“እንደ አንድ ጨዋታ ነጥቡ ያስፈልገናል። ከዛ በዘለለ ደግሞ ደርቢ ነው። የደርቢ ጨዋታዎችን ማሸነፍ የሚፈጥረው በራሱ የሚያመጣቸው መልካም ነገሮች አሉ ፤ ቡድኑ ላይ ተነሳሽነትም ይፈጥርልሃል። ደጋፊዎቻችንን ከዚህ በፊት በውጤት ማጣት ምክንያት አስከፍተናቸዋል ፤ ደስተኞች አይደሉም። ያን ነገር የፈጠርነው እኛ ነን ስለዚህ በዚህ ጨዋታ ላይ ውጤታማ ሆነን ደጋፊዎቻችንን መካስ እንፈልጋለን። ስለዚህ ጨዋታው ብዙ ጠቀሜታ አለው። አንደኛ ያለንበት ደረጃ ኢትዮጵያ ቡናን የሚመጥን አይደለም። ስለዚህ ከዛ ደረጃ መውጣት አለብን አቅማችንን ማውጣት አለብን በዚህ ደረጃ ተነጋግረን መግባባት ላይ ደርሰናል ፤ ሜዳ ላይ እየሠራን ነው። ከእግዚአብሔር ጋር የሚሆነውን እናያለን።”

ደርቢውን ማሸነፍ ለቀጣይ ጨዋታዎች የተለየ ፋይዳ ይኖረዋል…?

“በሚገባ ይኖረዋል! የሚፈጥረው የሚያመጣቸው መልካም ነገሮች አሉ ተጫዋቾቹ ላይ ተነሳሽነትን ይፈጥርልናል። ያለውን መንፈስ ያነሳሳልናል። ስለዚህ እኛ የምንችለውን ነገር እንሰጣለን እንደ ተርኒንግ ፖይንት እንዲሆነን እንፈልጋለን አሁን ካለንበት የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ መውጫ ማድረግ እንፈልጋለን እና በዛ ስሜት ነው። ያ ማለት ተጨንቀን እንገባለን ሳይሆን ጨዋታው በሚፈልገው ደረጃ ያለንን ነገር መስጠት ያለብንን ነገር ሁሉ ሜዳ ላይ መወርወር አለብን እና በዛ ደረጃ ነው እየተዘጋጀን ያለነው።”

የቅዱስ ጊዮርጊስን የዘንድሮ አመጣጥ እና እንቅስቃሴ እንዴት አየኸው…?

“ያው ጥሩ ቡድን ነው። ተጫዋቾች ቢለቁባቸውም አሁን ያሉት ወጣቶቻቸው ጥሩ ነገር እየሠሩ ነው ያሉት። ጥሩ ቡድን ነው። በዛ ልክ ለተጋጣሚያችን ክብር አለን። ከዛ በተረፈ ግን ከእኛ ጋር ባለው ነገር ነው ጨዋታውን ማሸነፍ የምንፈልገው እና የራሳችን ላይ ነው ትኩረት አድርገን የምንገባው።”

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ታክቲካሊ በምን ልንፈተን እንችላለን ብላችሁ ታስባላችሁ…?

“እሱ የእኛ የራሳችን የቤት ሥራ ነው። በዛ ደረጃ የእነርሱን ቪዲዮዎች ለማየት ሞክረናል። ጠንካራ እና ደካማ ጎናቸውን ለማየት ሞክረናል። ከዛ በተጨማሪም ሜዳ ላይ እየሠራን ነው እና ትልቁ ግን እነርሱ ይዘውት ከሚመጡት በላይ እኛ የምንቀርብበት የጨዋታ መንገድ ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ።

የውጤት ግምትህ…?

“እኛ ለማሸነፍ ነው ሙሉ ለሙሉ እየተዘጋጀን ያለነው። ከወሬ በዘለለ አሸንፈን ከላይ የተናገርኳቸውን ነገሮች መቀየሪያ እንፈልጋለን። አንደኛ ካለንበት ካለንበት ደረጃ መውጣት አለብን ሁለተኛ የቡድናችን የማሸነፍ ስነልቦና መመለስ አለበት። ከዛ አንጻር ተከላክለን አቻ ምናምን የሚል እሳቤ ውስጥ አንገባም። ያለንን ወርውረን ለማሸነፍ ነው ውጤቱን እግዚአብሔር ያውቃል።”