አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ አስቀድሞ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል

👉 “የሁለቱም ቡድኖች ጨዋታ የራሱ የሆነ ቃና አለው”

👉 “ትኩረት ሰጥተን ጥሩ ነገር ለማድረግ ሥራችንን ጨርሰናል።”

👉 “ብዙ ደጋፊዎች ይመጣሉ ብዬ አስባለሁ።

በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ታሪካዊው ደርቢ ነገ በአዳማ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ይከናወናል። ሰኮር ኢትዮጵያም ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞችን ስለጨዋታ ያደረጉትን ዝግጅት ስለ ደርቢው ስሜት እና ስለሚገምቱት ውጤት እና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ያደረገነውን ቆይታ በቅድሚያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

የደርቢው ጨዋታ ከአዲስ አበባ ውጭ ስለመሆኑ ?

“ትልቅ ጨዋታ ነው ፤ በኢትዮጵያ ቡና እና በቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል የሚደረገው ደርቢ ከሌሎቹ የተለየ በጣም ትልቅ ስሜት እና በጣም ትልቅ የሆኑ ብዙ ነገሮች ያሉበት ነው። ነገር ግን ያው ደርቢ ሆኖም ከተማችን ላይ አይደለም የምንጫወተው እና ያ ነገር ትንሽ ስሜቱን ያቀዘቅዘዋል። በሁለታችን መሀል በሚደረግ ጨዋታ ያለው ጉልበት፣ የሚሰጠው የጨዋታው ትኩረት ከደጋፊም ሆነ ከማንኛውም ሚዲያው፣ ሕዝቡ ፣ ለድጋፍ የሚመጣው ፤ የሚደረጉ የተለያዮ ትዕሪቶች ሁሉ ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ሲጫዎት ይህንን ነበር የምናየው። አሁን ግን ከከተማችን ውጪ ነው አዳማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ከተማ ቢሆንም ያን ያህል ደጋፊ ይመጣል ወይ? እነዛ ተጽዕኖዎች ባይኖሩ ትልቅ ደርቢ ነበር ብዬ ነው የማስበው።”

የደርቢው ጨዋታ ምን ያህል ዋጋው ከፍ ያለ ነው…?

“የትኛውም አሥራ አምስቱም ቡድን ሲመጣ የምንሰጠውን ትኩረት የምንሰጠው ነው። ለጨዋታው ያለን ግነት ደርቢም ነውና ለዛ ትልቅ ዝግጅት አድርገን የተሻለ ነገር ለማድረግ ጥሩ ሥራ ሠርተናል። ከእግዚአብሔር ጋር ጥሩ ነገር እናደርጋለን ብዬ አስባለሁ። የተለየ ነገር የለውም ሁሉም ቡድን ከእኛ ጋር ሲጫወት ያለውን 200% ነው የሚሰጠው እኛም ትኩረት ሰጥተን ጥሩ ነገር ለማድረግ ሥራችንን ጨርሰናል።”

የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ቡና አመጣጥ እንዴት ትገመግመዋለህ…?

“ጥሩ ቡድን ነው። ጠንካራ ጨዋታ እንደሚሆን አስባለሁ። ለጠንካራ ጨዋታ የሚሆን ዝግጅትም አድርገናል ፤ ያንን ነው እየጠበቅን ያለነው።”

ከወቅታዊ ውጤት አንፃር ኢትዮጵያ ቡና ውጤት ዕርቆታል ይህ መሆኑ በነገው ጨዋታ ግምታቹ ዝቅተኛ ይሆን ?

በፍፁም !! እኛ ጊዮርጊስ ነን ለየትኛውም ቡድን የምንሰጠው ግምት እኩል ነው። ዝቅተኛ ግምት የሚባል አናቅም። ቡና በአሁን ሰዓት ውጤቱ ጥሩም ሆነ አልሆነም ለእኛ ብዙም የሚያሳስበን ነገር አይደለም። ለዚህ ጨዋታ ከፍተኛ ግምት ሰጥቶ እንደሚመጣ ነው የምናቀው። እግርኳስ በዕለታዊ አቋም የሚወሰን በመሆኑ ተገቢ የሆነ ትኩረት አድርገን ወደ ሜዳ እንገባለን።

ከሌሎቹ ጨዋታዎች የደርቢው ጨዋታ ላይ ታክቲካሊ በምን ልትፈተኑ ትችላላችሁ…?

“ትልቁ ነገር ደርቢ መሆኑ ነው። የሁለቱም ቡድኖች ጨዋታ የራሱ የሆነ ቃና አለው እና ያ ነገር ትልቅ ነው። በሁለቱም በኩል በደጋፊ ፊት ነው የምንጫወተው ብዙ ደጋፊዎች ይመጣሉ ብዬ አስባለሁ። ታክቲካል ነገሩ ላይም በትኩረት ለመሥራት እና ማድረግ ያለብንን ለማድረግ ነው የተዘጋጀነው።”

የጨዋታ ግምትህ…?

“ለማሸነፍ እና ጥሩ ነገር ለመሥራት ነው ነገ ወደ ጨዋታው የምንገባው።”