የፊት አጥቂው አቤል ያለው ሰለ ነገው ጨዋታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል

👉 “ለማሸነፍ ነው ወደ ሜዳ የምንገባው።”

👉 “ጊዜው ገና ነው ፤ አሁን ላይ ሆኖ እንዲህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም።”

👉 “የቡድናችን ጥሩ መሆን ነው እኔንም ጥሩ ያደረገኝ።”

የነገውን የሸገር ደርቢ ጨዋታን አስመልክቶ ከዚህ በፊት ባስነበብናችሁ ፅሁፍ ስለ ጨዋታው ያላቸውን ዝግጅት አስመልክቶ ከሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ጋር ያደረግነውን ቆይታ አጋርተናችሁ ነበር። አሁን ደግሞ በሁለቱ ቡድን ውስጥ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፉ ከሚገኙ ተጫዋቾች ጋር ቆይታ አድርገናል። የሊጉን ውድድር በስምንት ጎሎች በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየመራ ከሚገኘው አቤል ያለው ጋር በሸገር ደርቢ ጨዋታ እና በወቅታዊ አቋሙ ዙርያ ያደረግነውን አጭር ቃለ መጠይቅ እንዲህ አቅርበነዋል።

እያሳለፈ ስለሚገኘው ጥሩ አቋም…?

“ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው ፤ ይሄም የቡድን ሥራ ውጤት ነው። ብቻዬን ያሳካሁት ነገር የለም። የቡድናችን ጥሩ መሆን ነው እኔንም ጥሩ ያደረገኝ። ያው እኔ ለራሴ ብዙም ትኩረት አልሰጥም ቅድሚያ ለቡድኔ ነው። የኔ ጥሩ መሆን ብቻ አይደለም። ለዚህም የቡድን አጋሮቼን ፣ ደጋፊዎችን አጠቃላይ የቡድኑን አባላት ማመስገን እፈልጋለሁ። በቀጣይም በምችለው አቅም ቡድኔን ውጤታማ ለማድረግ ጠንክሬ እሠራለሁ።”


ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ስለመጨረስ…?

“ጊዜው ገና ነው ፤ አሁን ላይ ሆኖ እንዲህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። እንደ ማንኛውም አጥቂ አስባለሁ። አሁን ከመስመር አጥቂ ወደ ፊት አጥቂነት እየመጣሁ በመሆኑ ጎል ማግባት ይጠበቅብኛል። ነገ የት እንደሚያደርሰኝ የሚታይ ቢሆንም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ የማጠናቀቅ ሀሳብ አለኝ።”

ስለ ሸገር ደርቢ…?

“ትኩረት ሰጥተን በደንብ እየተዘጋጀን ነው። እንደሚታወቀው የደርቢ ጨዋታ ማሸነፍ ትልቅ ትርጉም ስላለው ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ለመውሰድ እየተዘጋጀን ነው።”

ጥሩ ወቅታዊ አቋማቸው በደርቢው የተሻለ የማሸነፍ ስነ ልቦና ይዘው እንዲገቡ ያለው አስተዋጽኦ…?

“ያው አንዳንዴ እግር ኳስ ያለፈው ሳይሆን ዕለታዊ የጨዋታ ብቃትህም ውጤቱን ይወስነዋል ፤ የባለፈው ወቅታዊ አቋም ጠቀሜታ ቢኖረውም በቂ አይደለም። ግን እኛ ግዴታም ማሸነፍ ስላለብን ለማሸነፍ ነው ወደ ሜዳ የምንገባው።”

የሸገር ደርቢ የማይረሳው ጨዋታ…?

“ከሁለት ዓመት በፊት አዳማ ላይ አራት ለባዶ ያሸነፍንበት ጨዋታ ፤ ግብ ስላስቆጠርኩ ከዛ በተጨማሪ ድባቡ ማራኪ የነበረ በመሆኑ እሱን ጨዋታ አልረሳውም። ጥሩ ትዝታ አለኝ።”