የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ መድን 0-1 ሲዳማ ቡና

“ምንም ልትገልፀው አትችልም በጣም ከባድ ነው” አሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌ

“በሚገባ ሰርተን መጥተናል ያ በመሆኑ ውጤታማ መሆን ችለናል” አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው

ሲዳማ ቡና በአዲሱ አሰልጣኝ መሪነት በኢትዮጵያ መድን ላይ ካስመዘገቀው ድል መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱም አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌ – ኢትዮጵያ መድን

በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ ሆነው ግን አሸንፈው አለመውጣታቸው …

“ምንም ልትገልፀው አትችልም በጣም ከባድ ነው ፣ ግራ ገብቶናል እንግዲህ የምንችለውን ያህል ተዘጋጅተን ነበር የመጣነው አንዳንድ ጊዜ እግር ኳስ በጠበከው ልክ ወይም በሰራህው ልክ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ እኛ አሁን ምንም እንኳን ወደ ጎልም ብንጠጋም በመያዝም በኩል የተሻልን ብንሆንም አጥጋቢ አይደለም ለእኔ እኔ ግራ ገብቶኛል ለራሴ በጣም የሚገርም ነው አንዳንድ ጊዜ ትዝታ ሆኖብህ የሚመጡ ነገሮች አሉ አይደለ እንደዛ በጣም አስገራሚ ነው።”

በጣም አስፈሪ የነበረው ኢትዮጵያ መድን ምን ጎደለው በተለይ በቅርብ ጨዋታዎች ?

“የጎደለውማ የሰው ኃይል ነው። በሰው ኃይል ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ ተጫዋቾች የሉንም በተመሳሳይ አቅም ላይ ያሉ ካለፈው የመጡ ከከፍተኛ ሊግ የመጡ ተመሳሳይ ተጫዋቾች ናቸው ያሉት በጣም ጥቂቶች ደግሞ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ብዙም በትክክለኛው አቅም ላይ ወይም ደግሞ በአቅማቸው አሉ ብለህ የምትላቸው አይደሉም ይሄ ይሄ ተደምሮ ማለት ነው። እኛን አሁን የስኳዱ ጥልቀት የሰው ሀይል አለው ግን ስታንዳርዱን የጠበቀ የለውም ውጤትን የሚቀይር ተጫዋቾችን ማጣታችን በራሱ አንድ ትልቅ ችግር ነው።”

ለሁሉም ተመልካች ማራኪ የሆነውን ኢትዮጵያ መድን መቼ እንጠብቀው ?

“በዚህ አይነት ከባድ ነው አስቸጋሪም ነው። ትላንት አንድ ነገር ስንል ነበር ከትላንት ወዲያም እንደዚሁ ግን ተመሳሳይ አይነት ነው እኔ አሁን በፍፁም ባለፈው የመከላከያ ጨዋታ የነበረን ዝግጅት የነበረንን ተነሳሽነት ስታይ በፍፁም በፍፁም ሌላ ቡድን መሰሎ ነው የቀረበው የመጀመሪያ አጋማሽ ከዕረፍት በኋላ በጣም የተሻለ ነገር ተመሳሳይ ነው አሁንም በዝግጅት ደረጃ ብታየው ትልቅ ትልቅ የምንሰራቸው ስራዎች ላይ ጥሩ ነገር ያደርጋሉ ግን አሁን እዚህ ላይ ስታያቸው ደግሞ ይሄ እግር ኳስ ይዞት የማመጣው ነገር አለ አይደል በራስ መተማመን የማጣት እነዚህ እነዚህ ተደማምረው ይዘውት የሚመጡት ነገሮች ስህተቶች ይጎላሉ ፣ በቃ የሚያቁትን ነገር በሙሉ መስራት እያቃታቸው ነው።”

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ሲዳማ ቡና

ከረጅም ጊዜያት በኋላ በመመለስ ድል ስላደረጉበት የመጀመሪያ ጨዋታቸው…

“ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር የነበረው ፣ ምክንያቱም የእኛ ቡድን ከዚህ ቀደም ወላይታ ድቻን አሸንፎ የመጣ ስለሆነ ያን ሞራል የማስቀጠል መልካም ነገር ይዘን የመከተል ሀሳብ ነበር የነበረን ፣ በዛ ሂደት ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ መድን በአብዛኛው በመስመር ጨዋታ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ለመመልከት ሞክረናል። ከዚህ ቀደም የነበሩ አንዳንድ ፊልሞችን ለማየት ሞክረናል ፣ የተጫዋቾችን ባህሪ በመቀጠል ባለሙያውም ትልቅ ባለሙያ በመሆናቸው ምን አይነት አጨዋወት ሊሆን እንደሚችል እረዳለሁ እና ያን ከማቆም አንፃር በተቃራኒው ደግሞ መጀመሪያ የሚቀድመው ያንተ ቡድን ጥንካሬ ስለሆነ በዛ ልክ በሚገባ ሰርተን መጥተናል ያ በመሆኑ ውጤታማ መሆን ችለናል።”

በሁለቱም አጋማሾች የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ስለነበሩ መቀዛቀዞች…

“የሁለተኛው የሚጠበቅ ነው ምክንያቱም ቡድንህ እየመራ ነው ሰዓት ማባከን ላይ ነው እየጫወትክ ትኩረት የምታደርገው ይሄ የሚጠበቅ ነው። የመጀመሪያው ግን ታክቲካል የሆኑ ቅያሬዎችን እስከምናደርግ ድረስ የፈለግነው ነገር አላገኘንም በተለይ በመስመር ተጫዋቾቻችን በኩል መጠነኛ መቀዛቀዝ ነበረ ፣ ያ መቀዛቀዝ እንደ ቡድን በአጠቃላይ መቀዛቀዝን ፈጥሯል።”

ከዚህ በፊት በነበረው አጨዋወት ልክ ውጤትን ይዤ ወጥቻለሁ ማለት ይቻላል ?

“አይ እንደዛ ማለት አይቻልም። የማይቻለው ለምንድነው ከዚህ ቀደም በጥብቅ መከላከል ላይ ያተኮረ ቡድን ነበር የነበረኝ አሁን ግን ይሄ እኔ የሰበሰብኩት ቡድን አይደለም። እኔ ወደ እነርሱ መምጣት ነው የሚቀለው እንጂ እነርሱን ወደ እኔ ማምጣት ይከብዳል ስለዚህ እኔ ወደ ተጫዋቾቹ መጥቼ እነርሱ በሚጫወቱት ባህል ነው ያካሄድከት ምክንያቱም አሁን ያን መነሻ አድርገህ ስትመለከት ከዕረፍት በፊትም ከዕረፍት በኋላም በግብ ሙከራዎች የተሻልን የነበርነው እኛ ነን ይሄ ደግሞ ምናልባት አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠራችን በጥሩ መከላከል አንድ አግኝተን ሊመስል ይችላል ፣ ነገር ግን ከዕረፍት በፊትም ከዕረፍት በኋላም በርካታ የማዕዘን ምቶችን ነው ያገኘነው እኛ ነን ወደ ግብም የሞከርነው ሙከራዎችን ያደረግነው እኛ ስለሆንን የመጀመሪያው ማንነት አለ ሳይሆን እኔ ወደ እነርሱ የተመለስኩበት ሂደት ነው ያለው።”

በመጀመሪያ ጨዋታው ስለማሸነፋቸው እና ስለ ቀጣይ ዕቅዳቸው…

“ከቡድኑ ጋር እንግዲህ ሰፊ ደጋፊ አለው ፣ ተወዳጅ ክለብ ነው። ከዛም በተጓዳኝ ደግሞ ስብስቡ ብዙም እንከን የማይወጣለት ጠንካራ ስብስብ ነው ያለው በዛ ላይ መጠነኛ መሸጋሸጎች የሚደረጉ አሉ ጥቂት የሚባሉ ክፍተቶችም አሉ እነዛን ደፍነን ወደ ውጤት የምንጓዝበት ሂደት ስላለ በቀሪው እያሸነፍን ስለመሄድ ነው የምናስበው። የዛሬውን ጨዋታ አድርገናል ለእኔ ዛሬ ነው የጀመርኩት ሊጉንም ዛሬ ነው የጀመርኩት ስለዚህ ልጆቹ ላይ ያሰረፅኩት መንፈስ ምንድነው ለዋንጫም እንጫወት ወይም ለደረጃ እንጫወት ነገር ግን የዛሬን ጨዋታ አሸንፈን ከዛሬ በኋላ ደግሞ ከፊት ያሉትን እያሸነፍን ስለመሄድ ነው ያሰብነው።”