ሪፖርት | ነብሮቹ ተከታታይ ድል ተቀዳጅተዋል

በምሽቱ መርሐግብር አዳማ ከተማን የገጠሙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሠመረ ሀፍተይ ብቸኛ ግብ 1ለ0 በመርታት ተከታታይ ድል አሳክተዋል።

በምሽቱ መርሐግብር አዳማ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ተገናኝተዋል። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች ከስምንተኛ ሳምንት የሊግ ጨዋታቸው አዳማ በሁለት ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ በአንድ ተጫዋቾች ላይ ቅያሪ አድርገዋል። አዳማ ቻርለስ ሪባኑ እና ነቢል ኑሪን አሳርፎ በኤልያስ ለገሠ እና ቦና ዓሊ ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ ቃልአብ ውብሸትን አሳርፎ በዳግም ንጉሤ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ በቅርቡ በድንገተኛ አደጋ ሕይወቱ ላለፈው የአዳማ ከተማ የረጅም አመት ደጋፊ ለሆነው አብነት መታሰቢያ የሕሊና ጸሎት በማድረግ በተጀመረው ጨዋታ አዳማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢወስዱም ሀዲያዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሰመረ ሀፍተይ ከቀኝ መስመር የተነሳውን ኳስ በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ነብሮቹ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በመጫወት በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ፍላጎት ሲየዩ አዳማዎች በአንጻሩ በጥሩ የኳስ ቁጥጥር ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ 15ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ጀሚል ያቆብ ያሻገረለትን ኳስ ቦና ዓሊ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ለማመቻቸት ሲሞክር ከኋላ የመጣው ቢኒያም ዓይተን ሳይጠበቅ ወደ ግብ መትቶት ግብ ጠባቂው ታፔ አልዛየር ይዞበታል።

30ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ለገሠን በጉዳት በማጣታቸው ሙሴ ኪሮስን ቀይረው ያስገቡት አዳማዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ሲታትሩ 37ኛው ደቂቃ ላይ የአጋማሹን የተሻለ ሙከራቸውን አድርገዋል። ቢኒያም ዓይተን በሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ በግሩም ሩጫ የወሰደውን ኳስ ወደ ውስጥ አሻምቶት ቦና ዓሊ ተገልብጦ ያደረገው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል። 43ኛው ደቂቃ ላይም ቢኒያም ዓይተን በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ወደ ግብ ለመምታት በሚመስል መልኩ ያሻገረውን ኳስ ሳያገኙት ቀርተው የግብ ዕድላቸውን አባክነውታል። ጉዳት ያስተናገደው ኤልያስ ለገሠም ለተጨማሪ ሕክምና በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል አምርቷል።

ከዕረፍት መልስም አዳማዎች በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ፍጹም ብልጫ በመውሰድ እጅግ በጋለ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን መድረስ ቢችሉም በከድር ኩሊባሊ የሚመራውን የሀድያ የተከላካይ መስመር ጥሰው ግብ ለማስቆጠር ተቸግረዋል። ሆኖም ግን 59ኛው ደቂቃ ላይ ሀይደር ሸረፋ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረው ኳስ ሳጥን ውስጥ በስሱ ተጨርፎ መረቡ ላይ አረፈ ሲባል በግቡ የቀኝ ቋሚ ለጥቂት ወጥቷል።

በተደራጀ የመከላከል እንቅስቃሴ የአዳማን ጥቃት መመከት የቻሉት ሀድያዎች በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች በመጠኑ ወደ ፊት ተጠግተው ለመጫወት ሲሞክሩ 73ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሠመረ ሀፍተይ በድንቅ ሩጫ የወሰደውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ተቀይሮ የገባው ሪችሞንድ ኦዶንጎ ኳሱን ሳይቆጣጠረው ቀርቶ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

መጠነኛ ፉክክር በተደረገባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች ነብሮቹ 90ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ወርቃማ ዕድል አግኝተው ነበር። መለሰ ሚሻሞ በግራ መስመር ግቡን ለቆ ከወጣው ከግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ በቀማው ኳስ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ሆኖም ጨዋታው በሀድያ ሆሳዕና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።