የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-1 ሀዲያ ሆሳዕና

“በተጋጣሚያችን እንቅስቃሴ ልክ ነው እኛም ተዘጋጅተን የመጣነው” አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ

“በጥድፊያ ከዚህ በፊትም አላገባንም አሁንም የሚመጣ ነገር የለም” አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ

በምሽቱ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና በሠመረ ሀፍታይ ብቸኛ ጎል አዳማ ከተማን ካሸነፈ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞች ጋር ቆይታን አድርጋለች።

አሰልጣኝ ግርማ ታደሠ – ሀድያ ሆሳዕና

ስለ ጨዋታው …

“ጨዋታው አዳማ በጣም ኳስ ይዞ አደራጅቶ የሚጫወት ጠንካራ ቡድን ነው። በደንብ ነው ተዘጋጅተን የመጣነው ፣ ብልጫ እንደሚወስዱብን እናውቃለን ኳስን በደንብ ፖሰስ አድርጎ የሚጫወት ቡድን ስለሆነ በዛው ልክ ነው በተጋጣሚያችን እንቅስቃሴ ልክ ነው እኛም ተዘጋጅተን የመጣነው ያንን አሳክተናል ብዬ አስባለሁ ፣ ለምን ስህተቶችን በጣም ይሳሳታሉ ፣ በራሳቸው ሜዳ ላይ ያን ስህተት ለመጠቀም ነበር ታርጌት በማድረግ የመጣነው ብዙ አጋጣሚዎች አግኝተናል ፣ ብዙ ተጨማሪ ጎሎችን የማግባት አጋጣሚ አግኝተናል ነገር ግን ቀድመን ያገባነው ጎል ጥሩ ስነ ልቦና ፈጥሮልናል እና አማራጮችን አግኝተናል ፣ አጋጣሚዎችንም መፈጠር ችለናል ግን አልተጠቀምንባቸውም እንደ አጠቃላይ ያለው ነገር ግን የጨዋታ ፍሰቱ የተሻለ ቢሆንም አዳማን እኛ ለማሸነፍ ታርጌት አድርገን የገባነውን በሚገባ አሳክተናል ብዬ አስባለሁ።”

አስራ ሦስት ሙከራ የተደረገበት እና ጠንካራ ስለ ነበረው የተከላካይ ክፍል ዝግጅት…

“በደንብ ተዘጋጅተን ነው የመጣነው፣ ዲፌንሲፍ ጨዋታችን በጣም የተሻልን ሆነን መቅረብን ነው የፈለግነው ለምን ባለን ጠንካራ ነገር ነው መጫወት የፈለግነው ፣ እነርሱ የተሻለ የኳስ ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾች አሏቸው እኛ ደግሞ በጣም ወርክ ሬት ተጫዋቾች አለን ስለዚህ መጠቀም ያለብን ሜዳችንን አጥበን የምናገኘውን አጋጣሚ ጎል ለማግባት ፕላን አድርገን ነው የመጣነው ጥሩ አጋጣሚዎችን ፈጥረናል። የማግባት አቅማችን አነስተኛም ቢሆን የጎል አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለናል በዕርግጠኝነት ለተመልካች ሳቢ ላይሆን ይችላል ነገር ግን ከውጤት አንፃር አቅደን የመጣንበት ነገር ስለሆነ አሳክተናል።”

ተከታታይ ድል ማስመዝገባቸው እና ክለቡ ከድሎቹ በፊት አጥቷቸው የነበሩ ነገሮች…

“እንደ ቡድን አጀማመራችን ትክክል አልነበረም። ችግሮች ነበሩ እነዛን ችግሮች ምንአልባት እኛ ከጀመርን በኋላ በስነ ልቦና ልጆቹ ብዙ ጥሩ አልነበሩም ፣ ስነ ልቦና ላይ ጥሩ ነገር ሰርተናል ፣ ሀላፊነት ሰጥተናቸዋል ፣ በሀላፊነት የተሻለ ነገር እንዲሰሩ በቂ ሀላፊነትም ነው የሰጠናቸው ተነሳሽነታቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። እኛም የሄድንበት መንገድ ምቹ ሁኔታን ነው የፈጠርንላቸው ሌላ አይደለም እነርሱ ያላቸውን አቅም እንዲጠቀሙ ያ ነው ውጤታማ እያደረግን የመጣው።”

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው …

“ጨዋታው ሁለት አይነት ገፅታ ነው ያለው ፣ ከዕረፍት በፊት እና ከዕረፍት በኋላ ያው እንዳየህው ነው እንግዲህ።”

በሁለቱም አጋማሾች ጎል ለማስቆጠር ስለ ነበሩ አለመረጋጋት እና ጥድፊያዎች…

“ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ስንደርስ ትንሽ መረጋጋት ይፈልጋል። በጥድፊያ ከዚህ በፊትም አላገባንም አሁንም የሚመጣ ነገር የለም እና ሦስተኛው ሜዳ ላይ ስንደርስ ትንሽ ጥድፊያዎች ነበሩ እነዚያ ጥድፊያዎች ደግሞ ዋጋ አስከፍሎናል።”

ከተጋጣሚ የመከላከል ጥንካሬ አንፃር ውጤት አጥተናል ማለት ይቻላል ?

“እንደዚህ አይነት ነገር ይዞ እንደሚመጣ የገመትነው ነው የሆነው ፣ በመልሶ ማጥቃት ነው መጫወት የሚፈልጉት ፊት ላይ ፈጣን ተጫዋቾች አሏቸው ጠንካራ ቡድን ነው። በእነዛ ልጆች መጠቀም እንዳለባቸው ይገባናል የገባው ጎል አንድ እንደታየው ነው። ከዛ በኋላ ብዙም ሙከራ የለም ፣ በሙሉ ሀይል ለማጥቃት ሞክረናል ያም ደግሞ አልተሳካም ዛሬ።”

ቢኒያም አይተን መሐል ላይ ስለ መጫወቱ እና የመጀመሪያ ጨዋታ ስላደረገው ሙሴ ኪሮስ…

“ሙሴ ወደ ፊት ትልቅ ተጫዋቾች የሚሆን ልጅ ነው። አንዳንዴ ዝም ብለህ ታዳጊ ይዣለሁ ብለህ ማለት ሳይሆን እንደዚህ ታዳጊዎችን እያስገባህ ዕድላቸውን እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው። ቢኒያም እዚህ ቦታ በፊትም ተጫውቷል አንድ ገብቶብናል ማግባት አለብን ፣ በይበልጥ በማጥቃት ነው መጫወት ያለብን የማጥቃት ሀይላችንን ከፍ ለማድረግ አራተኛ አጥቂ አድርገን ሦስት ዳር እና ዳር በማድረግ እሱ ተደርቦ እንዲጫወት ነው የሞከርነው እና ሌላ የተለየ ነገር የለውም።”

ከሦስት ጨዋታዎች እስከ አሁን አንድ ነጥብ ብቻ ስለ ማግኝታቸው…?

“ውድድሩ ገና ነው ጨዋታዎችን እያሻሻልን ወደ ፊት ተጋጣሚያችንን ሳይሆን የራሳችን አጨዋወት ላይ ትኩረት አድርገን ቀጣይ ጨዋታዎችን አሸንፈን ማራቶኑን መከተል ነው።”