መረጃዎች | 35ኛ የጨዋታ ቀን

በዘጠነኛው የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚደረጉ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎቹ በተከታዩ መልኩ ቀርበዋል።

ሻሸመኔ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ

በጨዋታ ዕለቱ የመክፈቻ መርሃግብር በሰንጠረዡ ሁለት ፅንፍ በተለያየ መንገድ እየተጓዙ የሚገኙትን ሻሸመኔ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማን ያገናኛል።

በሊጉ ገና በጊዜ የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ ክለቦች አንዱ የሆኑት ሻሸመኔ ከተማዎች አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስን ወደ ኃላፊነት ካመጡ በኃላ ምንም እንኳን ከተራራቁት ሙሉ ሦስት ነጥብ ጋር መታረቅ ባይችሉም በመጨረሻ ጨዋታቸው ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ ሁለት ከፍ ሲያደርጉ በጨዋታው ቡድኑ የነበረው እንቅስቃሴ ደግሞ መጠነኛ እምርታን ያሳየ ነበር።

በመከላከሉ ሆነ በማጥቃቱ ረገድ በሊጉ ፍፁም ደካማ ቁጥሮች ያሉት ቡድኑ ከአሰልጣኝ ለውጡ በኃላ ግን በእንቅስቃሴ ረገድ የመሻሻል ምልክቶችን እየሰጠ ይገኛል። በተለይም ቡድኑ ከኳስ ውጭ ያለው የመከላከል መዋቅር እየተሻሻለ የሚገኝ ሲሆን የማጥቃት ጨዋታቸው ግን አሁንም ብዙ ስራ የሚጠብቀው ይመስላል ፤ ለዚህም የሊጉ ውድድር ለቀናት መቋረጥ ለአሰልጣኝ ዘማርያም የተሻለ የመዘጋጃ ጊዜን የሚሰጥ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሊጉ ለዋንጫው በሚደረገው ፉክክር ውስጥ በብዙዎች ዘንድ ቀዳሚ ግምትን ያገኙት ባህር ዳር ከተማዎች የነገውን ጨዋታ ጨምሮ በቀጣይ ከሚያደርጓቸው ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች በወረቀት ደረጃ ድል በማድረግ ይበልጥ ወደ ሰንጠረዡ አናት የሚጠጉበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

በመጨረሻ ሦስት የሊግ ጨዋታቸው በተመሳሳይ የ2ለ1 ውጤት ተጋጣሚያቸውን መርታት የቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ እንደታዘብነው ቡድኑ ጨዋታዎችን በጥሩ መልኩ ቢጀምሩም በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻ 20 ደቂቃዎች ላይ ጨዋታዎችን ለመቆጣጠር ሲቸገሩ ብሎም በተጋጣሚያቸው ጫና ውስጥ ሲወድቆ እየታዘብን እንገኛለን።

በነገው ጨዋታ በሻሸመኔ ከተማዎች በኩል ቻላቸው መንበሩ ፣ ያሬድ ዳዊት እና እዮብ ገብረማርያም በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ በባህር ዳሮች በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ለነገ ዝግጁ ናቸው።

የጨዋታ ዕለቱ የመክፈቻ የሆነውን ይህን መርሃግብር በመሐል ዳኝነት ባሪሶ ባላንጎ ከኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ሙሉነህ በዳዳ ከአራተኛ ዳኛው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ጋር በጣምራ ይመሩታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መቻል

በሰንጠረዡ አናት ከመሪው በጥቂት ነጥብ ርቀው የሚገኙትን ቅዱስ ጊዮርሶችን ከመቻል የሚያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር በብዙዎች ዘንድ በትኩረት የሚጠበቅ ነው።

ከአስደናቂ የሊግ አጀማመራቸው ማግስት ከመጨረሻ ሶስት የሊግ መርሃግብራቸው በሁለቱ ሽንፈትን ያስተናገዱት ፈረሰኞቹ ከመሪዎቹ ላለመራቅ በነገው ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት የግድ ይላቸዋል። ከመሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአራት ነጥቦች ርቀት በአስራ ስድስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በአንፃሩ በሊጉ ባደረጓቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎችን በተከታታይ ማሸነፍ የቻሉት መቻሎች አሁን ላይ በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ነገም ይህን የማሸነፍ ጉዞ ለማስቀጠል ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ካለፉት ዓመታት አንፃር በቅዱስ ጊዮርጊስ ደረጃ በቂ የተጫዋቾች አማራጮች የሌላቸው ፈረሰኞቹ ከጨዋታዎች ነጥቦችን ይዞ ለመውጣት የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነውን አቤል ያለው ላይ ጥገኛ የሆኑ ይመስላል በአንፃሩ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ግቦችን እያገኙ የሚገኙት መቻሎች በዚህ ረገድ ግን የተሻለለ አፈፃፀም ባለቤት ናቸው።

ሁሌም ቢሆን ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን የሚያሳየው የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በርስ ግንኙነት በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶችን የተስተናገዱበት ሲሆን ነገም ሁለቱ ቡድኖች ካሉበት ሰሞነኛ ብቃት አንፃር ጠንካራ ፉክክር የሚያደርጉበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

በነገው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ቅጣት ላይ ከሚገኘው ሞሰስ አዶ ውጭ ሁሉም ተጫዋቾች ዝግጁ መሆናቸው ሲታወቅ በመቻል በኩልም በተመሳሳይ ቅጣት ላይ ከሚገኘው ግሩም ሀጎስ ውጭ ሁሉም ተጫዋቾች ዝግጁ ሲሆኑ በተለይም ከረጅም ጊዜ የጉዳት ቆይታ በኋላ በኢትዮጵያ ዋንጫ ዳግም ወደ ጨዋታ የተመለሰው ፍፁም ዓለሙ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑን ሰምተናል።

ሁለቱ ታሪካዊ ክለቦች ፕሪሚየር ሊጉ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 32 ጊዜ ተፋልመዋል። በጨዋታዎቹ 17 ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ 12 ጊዜ መቻል ደግሞ 3 ጊዜ አሸንፈዋል ፤ ፈረሰኞቹ 35 ጦሩ ደግሞ 17 ግቦችን ከመረብ አዋህደዋል።

12 ሰዓት ሲል ጅማሮውን የሚያደርገውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታን ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት በረዳት ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ወጋየሁ አየለ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ተሰይመዋል።