የአሰልጣኞች አስተያየት| ሀምበሪቾ 0 – 2 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

“ከገመትነውም በላይ የበለጠ መከላከል ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ነበራቸው”

“የጊዜ አጠባበቅ ችግራችንና የልምድ ጉዳይ ዋጋ አስከፍሎናል”

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ለባዶ አሸንፎ መሪነቱን ካጠናከረበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

አሰልጣኝ በፀሎት – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስለ ጨዋታው

ተጋጣሚያችን እንደጠብቅነው ነው ያገኘነው፤ ያለፉትን ጨዋታዎቻቸውን ተመልክተናል ወደዚ ጨዋታ ምን ይዘው ሊመጡ ይችላሉ ብለን እንደገመትነው አግኝተናቸዋል። ወደ ራሳቸው ግብ ተጠግተው ለመከላከል እንደሚጫወቱ ገምተን ነበር። በጣም መከላከል ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ነው የመረጡት፤ ሰባት የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ነው የተጠቀሙት። ከገመትነውም በላይ የበለጠ መከላከል ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ነበራቸው። ወደ ጨዋታው ከመግባታችን በፊት የተከላካይ ክፍሉ በምን መንገድ ማስከፈት እንችላለን በሚለው በጥልቀት ተነጋግረን ነው የገባነው። ጥቅጥቅ ብለው ስለሚጫወቱ ግብ ለማስቆጠር ተቸግረን ነበር፤ የማጥቃት ፍላጎታቸውን አናሳ ስለነበር ክፍት ቦታ ለማግኘት ከባድ ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በትእግስት ተጫውተን ግብ ማስቆጠር ችለናል። በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ስለተቆጠረባቸው በተወሰነ መልኩ ክፍል ቦታ እናገኛለን ብለን ገብተን በትእግስት ለመጫወት ሞከረን ውጤቱን ይዘን ወጥተናል።

ቡድኑ የሚጫወትበት ፍጥነት በሁለተኛው አጋማሽ ስለመቀዛቀዙ

ይሄ ከተፈጥሮም ከመርህም ህግ ውጭ ነው ። መጀመርያ አጋማሽ ላይ ተጋጣምያችን ያስገደደን ነገር አለ። ማንም ዓለም ላይ ያለ ቡድን በጀመረበት የጨዋታ ፍጥነት አይቀጥልም። ግብ ባናስቆጥር ኖሮ እንደጀመርንበት ፍጥነት መቀጠል እንችል ነበር። የአካል ብቃት ችግር የለብንም፣ ተጭኖ የመጫወት ችግርም የለብንም ይህ ጨዋታ የምንቆጣጠርበት መንገድ ነው። ይህ እንደ ድክመት የሚነሳ አይደለም።

ለዋንጫ የሚያደርጉት ጉዞ

ገና ዘጠነኛው ሳምንት ላይ ነን፤ ዘጠነኛ ሳምንት ላይ ሆነን ሀያ አንድ ጨዋታ እየቀረ፤ መጨረሻ ደረጃ ላይ ያለውና ሊጉን የሚመራ ቡድን ስለ ምንም ነገር ማውራት ይችላል ብዬ አላስብም። ጊዜው ገና ነው።

ብሩክ ሲሣይ – ሀምበሪቾ

ስለ ጨዋታው

በመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታው ለመቆጣጠር ሞክረናል፤ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ ግን በጊዜ አጠባበቅ ጎል ተቆጥሮብናል። ከዛ በኋላ ግብ ለማስቆጠር ከፍተን ሄደናል፤ ለቀን የሄድነው ክፍት ቦታ ተጠቅመውም ግብ አስቆጥረውብናል። በመከላከሉ ረገድ የተሻልን ነበርን ብዬ አስባለው። የጊዜ አጠባበቅ ችግራችንና የልምድ ጉዳይ ዋጋ አስከፍሎናል።


ስለ ነጥብ ልዩነቱ

ምንም አዲስ ነገር የለውም፤ እግር ኳስ ነው እንተርፋለን። ገና ዘጠነኛው ሳምንት ላይ ነው ያለነው። ጊዜ አለን ተነሳሽነት ካለ ብዙ የሚከብድ ነገር የለውም። የማሸነፍ መንፈስ አስፈላጊ ነው፤ ተደጋጋሚ ጊዜ ስትሸነፍ ግን መንፈሱ ይቀንሳል። ብዙ የተለፋባቸው ተጫዋቾች ናቸው ወጣቶችም ናቸው፤ ከከፍተኛ ሊግ ነው የመጡት። ከጨዋታ ጨዋታ ይሻሻላሉ፤ በጣም ጥሩ ቡድን ነው።