ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስድስተኛ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ንግድ ባንኮች ሀምበሪቾን 2ለ0 በመርታት መሪነታቸውን አጠናክረዋል።

ሀምበሪቾ ከኢትዮጵያ መድን ጋር በስምንተኛ ሳምንት ጨዋታውን ሲያደርግ ከተጠቀመው አሰላለፍ ውስጥ በስድስቱ ላይ ለውጥን አድርጓል። ብሩክ ቃልቦሬ ፣ አቤል ዘውዱ ፣ አቤል ከበደ ፣ ማናዬ ፋንቱ ፣ ቶሎሳ  ንጉሴ እና ኤፍሬም ዘካሪያስ ወጥተው ምንያምር ጴጥሮስ ፣ ታዬ ወርቁ ፣ ተመስገን አሰፋ ፣ በፍቃዱ አስረሳኸኝ ፣ ዳግም በቀለ እና በረከት ወንድሙ በሞትኩ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ኢትዮጵያ ቡናን ሲረታ በቀይ ካርድ ከሜዳ በወጣው ሱሌይማን ሀሚድ ምትክ አቤል ማሙሽን ተክቷል።

09፡00 ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በኳስ ቁጥጥሩ ፍጹም ብልጫ በመውሰድ እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ ተጭነው መጫወት ሲችሉ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሀምበሪቾዎች በአንጻሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት እና ጥቅጥቅ ብለው በመከላከል የባንክን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመጠኑ ለመመከት ጥረት አድርገዋል።

የመጀመሪያው ለግብ የቀረበ ሙከራም 27ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ የንግድ ባንኩ በረከት ግዛው ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ በድንቅ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም በረከት ግዛው ያሻገረለትን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው አቤል ማሙሽ ግብ ጠባቂውን ለማለፍ ጥረት ሲያደርግ ግብ ጠባቂው ፖሉማ በድጋሚ በግሩም ቅልጥፍና በግራ እግሩ አቋርጦበታል።

የተጋጣሚያቸውን የመከላከል አደረጃጀት ጥሰው ለመግባት ተደጋጋሚ ጥረት ያደረጉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 45ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። አዲስ ግደይ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ለብሩክ እንዳለ ያመቻቸውን ኳስ ብሩክ ወደ ግብ አክርሮ ሲመታው በተከላካይ ተመልሶበታል። የተመለሰውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው በአጋማሹ ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ባሲሩ ኦማርም በግሩም ብቃት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ሀምበሪቾዎች ከራሳቸው የግብ ክልል በቁጥር እየበዙ በመውጣት አጥቅተው ለመጫወት ሲሞክሩ ባንኮቹ በአንጻሩ ጨዋታውን በማረጋጋት መሃል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል። በአጋማሹ የተሻለው ሙከራም 60ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ አዲስ ግደይ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ኪቲካ ጅማ ተገልብጦ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ ይዞበታል።

በመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል ንግድ ባንኮች 79ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ቢኒያም ጌታቸው ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ሆኖ ወደ ያቀበለውን ኳስ ከማቀበል አማራጭ ጋር ሆኖ ያገኘው በረከት ግዛው በተረጋጋ አጨራረስ አስቆጥሮታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ንግድ ባንኮች ስድስተኛ ተከታታይ ድል አስመዝግበዋል።