መረጃዎች | 37ኛ የጨዋታ ቀን

በገና ዋዜማ የሚካሄዱ የዘጠነኛው ሳምንት መገባደጃ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ሀምበርቾ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የሊጉ መሪና በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ቡድን የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ ፍልሚያ ይሆናል።

አራት ተከታታይ ሽንፈቶች ያስተናገዱት ሀምበርቾዎች በሁለት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ ላይ ሆነው የሊጉን መሪ ይገጥማሉ። ሀምበርቾዎች ከወልቂጤ ከተማ ጋር በተመሳሳይ ዝቅተኛው የግብ መጠን ያስቆጠረ የማጥቃት ክፍል አላቸው፤
ከአዳማ ከተማ ጋር ሁለት አቻ ከተለያዩ በኋላ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎችም ኳስና መረብ አላገኙም። ከአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ስንብት በኋላ የመጀመርያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ሀምበርቾዎች በምክትል አሰልጣኞቹ መላኩ ከበደና ብሩክ ሲሳይ እየተመራ ወደ ጨዋታው ይቀርባል። አዲሱ የአሰልጣኞች ቡድን ለ 450 ደቂቃዎች ግብ ያላስቆጠረው አጨዋወት ከመቀየር በዘለለ አስራ ሦስት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ተጋጣምያቸው በስምንት ጨዋታዎች አስራ አራት ግቦች ያስቆጠረ ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ያለው መሆኑም ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

ሀያ ነጥቦች ሰብስበው በሊጉ አናት ላይ የተቀመጡት ንግድ ባንኮች መሪነታቸውን ለማጠናከር በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ሀምበርቾን ይገጥማሉ። ባንኮች በውድድር ዓመቱ ሽንፈት አልባ ጉዞ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፤ ማግኘት ከሚገባቸው ሀያ አራት ነጥቦች ሀያውን በማሳካትም በጨዋታ በአማካይ የላቀ ነጥብ በማስመዝገብ የሊጉ ቀዳሚ ናቸው። አሰልጣኝ በፀሎት በጊዜ ሂደት ሚዛኑ የጠበቀ ቡድን ገንብተዋል፤ በማጥቃትና መከላከሉ ላይ ያላቸው ውጤታማነትም የዚ ማሳያ ነው። አስራ አራት ግቦች አስቆጥረው አምስት ግቦች ብቻ ማስተናገዳቸውም የዚ ውጤት ነው። በተለይም ባለፉት አምስት ጨዋተዎች አስራ ሁለት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት ክፍል የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ ነው፤ በነገው ዕለትም በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስተናገደ ቡድን እንደመግጠማቸው

በንግድ ባንክ በኩል ሳይመን ፒተር እና ሱሌማን ሀምዲ በቀይ ካርድ ምክንያት የሉም። የባለፈው ጨዋታ ያልነበረው አጥቂው ቢንያም ጌታቸው ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው።

በመሐል ዳኝነት ጨዋታውን ሶሬሳ ካሚል ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ኤልያስ መኮንን ረዳቶች ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለሱስ ባዘዘው በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይሟል።

ወላይታ ድቻ ከ ወልቂጤ ከተማ

የዘጠነኛው ሳምንት መገባደጃ ጨዋታ በጦና ንቦቹ እና ሰራተኞቹ መካከል ይደረጋል።

ከተከታታይ ሁለት አቻና አንድ ድል በኋላ በመጨረሻው ሳምንት ሽንፈት የገጠማቸው ወላይታ ድቻዎች ከአስከፊው የአራት ለአንድ ሽንፈት ለማገገም ወልቂጤ ከተማን ይገጥማሉ። እስከ መጨረሻው የሊግ ጨዋታ ድረስ በሊጉ ጥቂት ግቦች ብቻ በማስተናገድ ፊት ላይ ከተቀመጡ ቡድኖች ውስጥ የነበሩት የጦና ንቦቹ ሲዳማ ቡናን በገጠሙበት ጨዋታ ግን ደካማ የመከላከል ብቃት አሳይተዋል፤ የዚህ ውጤትም በጨዋታው አራት ግቦች ለማስተናገድ ተገደዋል። የተከላካይ ክፍሉ ወደ ቀደመ ብቃቱ የመመለስ ስራም አሰልጣኙ ከሚጠብቃቸው የቤት ስራዎች አንዱ ነው። ምንም እንኳ በነገው ዕለት በስምንት ጨዋታዎች አራት ግቦች ብቻ ያስቆጠረ ደካማ የማጥቃት ጥምረት ያለው ቡድን ቢገጥሙም በመጨረሻው ጨዋታ የታየው የመከላከል አደረጃጀታቸው ግን ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ውጤቱ አመላካች ነው። ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑ የአጨራረስ ችግርም መፍትሄ የሚሻ ሌላው የቡድኑ ክፍተት ነው፤ ወላይታ ድቻዎች በተሰጥኦ የተሞላና የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የማይቸገር የአማካይ ክፍል ቢኖራቸውም ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ትልቅ ችግር ይስተዋልባቸዋል።

ተከታታይ ሁለት ድሎች አስመዝግበው ነጥባቸውን ወደ ስምንት ከፍ ካደረጉ በኋላ በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ በመቻል የሁለት ለባዶ ሽንፈት የገጠማቸው ወልቂጤዎች ይህንን ጨዋታ ካሸነፉ ብያንስ ሦስት ደረጃዎች የሚያሻሽሉበት ዕድል አግኝተዋል። በመቻል ሽንፈት በገጠማቸው ጨዋታ ላይ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በመከላከልና በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የሞከሩት ሰራተኞቹ በጨዋታው ጥሩ የሚባል የመከላከል አደረጃጀት ነበራቸው፤ ጨዋታው ምንም እንኳ ሁለት ለባዶ ቢጠናቀቅም በጥሩ ወቅታዊ አቋም ከሚገኙት መቻሎች ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ እስከ ሰማንያኛው ደቂቃ ድረስ ያደረጉት ተጋድሎ ግን ቀላል ግምት አይሰጠውም። አሰልጣኝ ሙልጌታ ምህረት አሁንም ጠንካራ አማካይና ጥሩ የማጥቃት አጨዋወት ካለው ቡድን ጋር እንደመጫወቱ በመጨረሻው ጨዋታ ከተከተለው አጨዋወት የተለየ አቀራረብ ይከተላል ተብሎ አይገመትም። ሆኖም ስንታየሁ መንግስቱ ላይ ያነጣጠሩ ረዣዥም ኳሶቻቸውና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ላይ ያላቸው አቅም ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል።

በወላይታ ድቻ በኩል አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙት አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ እና ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ ከነገው የጨዋታ ዕለት ስብስብ ውጭ ናቸው። በወልቂጤ በኩል ተስፋዬ መላኩ በቅጣት አይኖርም። የወንደማገኝ ማዕረግ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

ድቻ እና ወልቂጤ 6 ጊዜ ተገናኝተው ወልቂጤ ከተማ 3 ሲያሸንፍ ወላይታ ድቻ 1 አሸንፏል። 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ወልቂጤ 6 ሲያስቆጥር ድቻ 3 አስቆጥረዋል።

ዳንኤል ግርማይ ይህንን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ሲመራው ሙሉነህ በዳዳና ለዓለም ዋሲሁን ረዳቶች አባይነህ ሙላት ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል ።