የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህርዳር ከተማ 0-0 ሀምበርቾ

“ለተመልካች ምቾት የሚሰጥ ጨዋታ አይደለም” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው

“አንድም ነጥብ ቢሆን ቡድንህን ያነሳሳል” አሰልጣኝ ብሩክ ሲሳይ

በምሽቱ ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ እና የተራራ አናብሥቶቹ ያለ ጎል ካጠናቀቁት ጨዋታ መቋጫ በኋላ የድህረ ጨዋታ አስተያየትን ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞቹ ጋር አድርጋለች።

አሰልጣኝ ብሩክ ሲሳይ – ሀምበርቾ

ከአምስት ተከታታይ ጨዋታ በኋላ አንድ ነጥብ ስላገኙበት ጨዋታ…

“በመጀመሪያው አጋማሽ ገና ሀያኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ሰው ወጣብን ፣ ከዛ በኋላ የነበረንን ነገር ለመለወጥ ነው የሞከርነው። አስበን ከገባነው ነገር አንድ ሰው ሲጎልብህ ትለውጣለህ ወደ መከላከሉ እና ወደ ራሳችን ሜዳ ኳሱን ለቀን ለመምጣት አስበን ያንን አድርገን ወጥተናል።”

ቡድኑን ከተረከብክ በኋላ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ቡድኑ ላይ ምን ጨምሪያለሁ ብለህ ታስባለህ…

“ነጥብ ስትፈልግ ነጥብም ሲርቅህ ነጥብን ትፈልጋለህ ፣ አንድም ነጥብ ቢሆን ቡድንህን ያነሳሳል ፣ ሽንፈት እንደምታውቀው ነው የማሸነፍ አስተሳሰብህ እየወረደ ይመጣል ያንን ለማሻሻል ብለን አንድን ነጥብ አስበን አብዛኛውን ዲፌንሲቭ የሆነ ነገር አስበንም ገብተናል ያው ተሳክቶልናል። ሁለተኛ ምንድነው የተቃራኒ ቡድን አጨዋወቱ ጥሩ ኳሊቲ ያላቸው ተጫዋቾች አሉ ያንን ለመከላከል አስበን ሠርተን የመጣነው ይሄ ነው።”

ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ጎል አለማስቆጠራቸውን ተከትሎ በቀጣይ በአጥቂ ቦታ ላይ ምን ይጠበቃል…

“ከዚህ በፊት ብዙ ተደጋጋሚ ሙከራዎች የሚያደርግ ቡድን ነበር። የተቃራኒ ቡድን አካባቢ ብዙ እንሞክር ነበር። አሁን ላይ ግን ተከታታይ የተጫወትናቸው ቡድኖች ትንሽ ጠንከር ያሉ በሊጉም ደረጃ ላይ ትንሽ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ያሉ ቡድኖች ስለሆኑ እነርሱ ላይ ያንን ዓይነት አጨዋወት ይዘን መግባት አንችልም ያንን አላደረግንም ግን ከዚህ በኋላ ደግሞ መከላከሉ ላይ ጥሩ ነን ማጥቃቱን ደግሞ አሻሽለን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ።”

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ

በኳስ ቀጥጥርም ሆነ በሙከራ የተሻሉ ሆነው ያለ ጎል ስለፈፀሙት ጨዋታ…

“ለተመልካች ምቾት የሚሰጥ ጨዋታ አይደለም። ዲስትራክቲቭ እግር ኳስ ነው የሚጫወተው ተጋጣሚ አንዱ ደግሞ ነፃ የሆነ ማጥቃት ላይ መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴን የሚጫወት ቡድን ነው ዛሬ ጨዋታቸውን ያደረጉት። እኛ ባለን አቅም በሙሉ አቅማችን አጥቅቶ ለመጫወት ነው ጥረት ስናደርግ የነበረው በአጠቃላይ በኳስ ብልጫም በይበልጥ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት ስናደርግ ነበር ነገር ግን እንደዚህ በሎው ብሎክ ወርዶ መጫወት ብቻ ሳይሆን ባለፈው እንዳልኩት እነዚህ ጨዋታን እያበላሹ የመጫወት እንቅስቃሴ ነበር በሜዳው ላይ ያለው ፤ ምንም ልታደርገው አትችልም ተጫዋቾቻችን የሚችሉትን በሙሉ ሞክረዋል ጥረት አድርገዋል። እግር ኳስ ውስጥ ብዙ ነገሮች ይፈጠራሉ እና ከዚህ አኳያ ጎል ማግኘት ነው ያልተቻለው በእንደዚህ አይነት ውስጥ እንዴት ጎል ማግኘት እንዳለብን በትዕግሥት ተጫውተን ነው ጎል ማግኘት የምንችለው ግን በይበልጥ ልጆቻችን ነርቨስ እየሆኑ የሚሄዱበት እንቅስቃሴው በራሱ ከሙድ የሚያወጣ እንቅስቃሴ ነበር የነበረው ፣ እንደ አጠቃላይ ተጫዋቾቼ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል ይሄንን መቀበል ነው።”

ሦስት ተከታታይ ጨዋታ ካሸነፉ በኋላ በሁለት ወራጅ ቀጠና ላይ ባሉ ቡድኖች በተከታታይ ነጥብ መጋራታቸው እና የቡድኑ የማጥቃት ኃይል መቀዛቀዙ…

“የሚገኙ አጋጣሚዎችን ወደ ጎል የመቀየር እንዲሁም ደግሞ የጎል ዕድሎችን መፍጠሩ ላይ ክፍተቶች እየታዩ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ያንን በቀጣይ ቀርፈን ለመቅረብ ነው ጥረት የምናደርገው በጉልህ ፣ በአንፃሩ በመከላከሉ ረገድ ጎል እንዳይቆጠርብን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት ፣ ተከታታይ ጨዋታዎችን ጎል ሳናስተናግድ የወጣንበት ሁኔታ ነው ያለው በአንፃሩ ግን ደግሞ ጎሎች ማግኘቱ ላይ ትንሽ የተቸገርንበት ሁኔታ እንዳለ በግልጽ የሚታይ ነው። በቀጣይ ጊዜያት ደግሞ እነዚህ ላይ ረርተን የተሻለ ነገር እናስመዘግባለን ብዬ አስባለሁ።”