መረጃዎች| 41ኛ የጨዋታ ቀን

የአስረኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ይገባደዳል፤ የዕለቱን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ በተመሳሳይ ሁለት ሽንፈቶች ያስተናገዱት ወልቂጤ ከተማዎች በስምንት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሰራተኞቹ በወላይታ ድቻ ሽንፈት በገጠማቸው ጨዋታ ላይ ከወትሮው ባለ አቀራረብ ነበር የቀረቡት፤ ቡድኑ ከመቻል ጋር ባካሄደው የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ በዋነኝነት መከላከል ላይ ያተኮረ አቀራረብ ይዞ ቢገባም በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ ግን ከሌላው ጊዜ በተሻለ ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት አድርጓል። አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በተከተለለው ተቀያያሪ አቀራረብ ምክንያት በነገው ጨዋታ የሚጠቀምበት አጨዋወት ለመገመት ቢያዳግትም ከተጋጣሚው የአማካይና የአጥቂ ጥንካሬ አንፃር ኳሱን ከመቆጣጠር ይልቅ ጠጣር አቀራረብ ይዞ ይገባል ተብሎ ይገመታል።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ድሬዳዋ ከተማን ሦስት ለባዶ ያሸነፉት አፄዎቹ በአስራ አምስት ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ፋሲሎች ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት ባደረጓቸው ጨዋታዎች ላይ በጉልህ የታየባቸው የግብ ማስቆጠር ችግር ፈተዋል፤ ቡድኑ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ላይ ምንም እንኳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢያስመዘግብም የተጋጣሚን የተከላካይ ክፍል አልፎ ዕድሎች መፍጠር ላይ መጠነኛ ክፍተቶች ነበሩት። ድሬዳዋ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ግን ይህንን ችግር ከመቅረፍ ባለፈ ጥሩ የቡድን ስራ የታየቧቸው ግቦች አስቆጥረዋል። ከዚ ባለፈ ቡድኑ ከቆሙ ኳሶች ያደረጋቸው ሙከራዎችና ያስቆጠሩት አንድ ግብ ቡድኑ ሌላው የግብ ማግኛ መንገዶች እንዳበጀ ማሳያዎች ናቸው። ሆኖም የነገው ተጋጣሚያቸው በሰባተኛውና ስምንተኛው ሳምንት ላይ ቡድኑ ከገጠማቸው ጠጣር ቡድኖች የሚመሳሰል አቀራረብ ይዞ ይቀርባል ተብሎ ስለሚገመት በመጨረሻው ጨዋታ ላይ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል የነበራቸው ውጤታማነትና ጥሩ ውህደት ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።

በወልቂጤ ከተማ በኩል ተስፋዬ መላኩ እና ሳምሶን ጥላሁን በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። ወንድማገኝ ማዕረግ ግን ከጉዳት ተመልሷል። በፋሲል ከነማ በኩል አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ እዮብ ማቲያስ፣ ፍቃዱ አለሙ እና ሸምሰዲን መሐመድ በጉዳት ምክንያት ነገ ከሚደረገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ስድስት ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ሦስት ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ያለ ጎል አቻ ተለያይተው አንድ ጨዋታ ወልቂጤ አሸንፏል። ፋሲል አራት ወልቂጤ ሁለት ጎሎች አስቆጥረዋል።

ሔኖክ አበበ በመሐል ዳኝነት ከረዳት ዳኞቹ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ሠለሞን ተስፋዬ እንዲሁም ከአራተኛ ዳኛው ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ጋር በጥምረት ይመሩታል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ወላይታ ድቻ

በዘጠነኛው ሳምንት ድል ያስመዘገቡና ጠንካራ የአማካይ ክፍል ያላቸው ቡድኖች የሚያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ የሳምንቱ ማሳረጊያ ይሆናል።

ስድስት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው በጥሩ ወቅታዊ አቋም ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ንግድ ባንኮች እግር በእግር ከሚከታተላቸው መቻል ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት ወላይታ ድቻን ይገጥማሉ። አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ በሁሉም ረገድ የተሟላና ሚዛኑን የጠበቀ ቡድን ገንብተዋል። በመከላከሉና በማጥቃቱ ያላቸውን ውጤታማነት ለመገንዘብ ያስመዘገቧቸው ቁጥሮች ማየት በቂ ነው። ቡድኑ በሊጉ ዝቅተኛ የግብ መጠን(5) ከማስተናገድ ባለፈ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ በርካታ ግቦች ያስቆጠረ(16) ክለብ ነው፤ እነዚ ቁጥሮችም ቡድኑ ምን ያህን ሚዛናዊ እንደሆነ ማሳያዎች ናቸው። ንግድ ባንኮች በሊጉ ምንም ሽንፈት ያልቀመሰ ብቸኛ ክለብ ነው፤ ከዛም አልፎ ተከታታይ ስድስት ድሎች በተቀዳጀባቸው ጨዋታዎች በጨዋታ በአማካይ 2.3 ግቦች አስቆጥሯል። በነገው ጨዋታ በዘጠኝ ሳምንታት አስር ግቦች ላስተናገደው የወላይታ ድቻ የተከላካይ ክፍል ትልቅ ፈተና ይሆናል ተብሎ ቢገመትም ከተጋጣሚው የአማካይ ክፍል ጥራት አንፃር የመሀል ሜዳ ብልጫ ለመውሰድ ቀላል ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ አይጠበቅም።

በዘጠነኛው ሳምንት ላይ ወልቂጤ ከተማን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ከአስከፊው ሽንፈት ቶሎ ያገገሙት ወላይታ ድቻዎች በአስራ አራት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፤ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ተከታታይ ድሎች ለማስመዝገብም ጠንካራውን ንግድ ባንክ ይገጥማሉ። የጦና ንቦች በሊጉ ጠንካራ የአማካይ ክፍል ካላቸው ቡድኖች ይመደባሉ፤ በነገው ጨዋታም ከሌላው ጠንካራ የአማካይ ክፍል ካለው ቡድን ጋር እንደመጫወታቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚደረገው ፍልምያ የጨዋታውን ውጤት ይወስነዋል ተብሎ ይገመታል። ከዛ በተጨማሪም ከውስን ጨዋታዎች ውጭ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ በማሳየት በጨዋታ በአማካይ 1.1 ግቦች ያስተናገደው የጦና ንቦች የተከላካይ ክፍል በጥሩ ወቅታዊ የግብ ማስቆጠር ብቃት ላይ ያለው የንግድ ባንክ ተከላካይ ክፍል እንቅስቃሴ የመግታት ትልቅ ሀላፊነት ይጠብቀዋል። በሊጉ የመጀመርያ ሳምንታት ላይ የግብ ዕድሎች የመጠቀም ችግር የተስተዋለበት የቡድኑ የአጥቂ ጥምረትም ምንም እንኳ በጊዜ ሂደት ጥሩ መሻሻል ቢያሳይም ጠንካራውን የንግድ ባንክ ተከላካይ ክፍል መፈተን የሚያስችል አቅም ማጎልበት ይኖርበታል።

በንግድ ባንክ በኩል ፍቃዱ ደነቀ በጉዳት አይሰለፍም፤ ቅጣት ላይ የነበሩ ሱሌማን ሀሚድና ሲሞን ፒተር ግን ቅጣታቸውን ጨርሰው ለጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በወላይታ ድቻ በኩል አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙት አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ እና ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ ከነገው የጨዋታ ዕለት ስብስብ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ስምንት ጊዜ የግንኙነት ታሪክ አላቸው። ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ በአራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ወላይታ ድቻ 9 ሲያስቅጥር ንግድ ባንክ 7 አስቆጥሯል።

በ2006 ወላይታ ድቻ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደረገው በአዲስ አበባ ስታዲየም ከባንክ ጋር ሲሆን 4-0 በማሸነፍ ከሊጉ ቤተሰብ ጋር ተዋውቋል።

ይህንን ጨዋታ በዋናነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አሸብር ታፈሠ ረዳት በመሆን ሲያገለግሉ አባይነህ ሙላት አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።