ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የዓመቱ ምርጥ ሴት ተጫዋች ሆና ተመረጠች

ከኢትዮጵያን ቤተሰቦች የተገኘችው ናኦሚ ግርማ የ ዩኤስ አሜሪካ ምርጥ ሴት ተጫዋች ተብላ በመመረጥ አዲስ ታሪክ ፅፋለች።

ከሳንድያጎ ዌቭና ከዩ ኤስ አሜሪካ ብሄራዊ ቡድን ጋር የተሳካ የውድድር ዓመት ያሳለፈችው ናኦሚ ግርማ በ2023 የፊፋ የሴቶች የአለም ዋንጫ ከዩኤስኤ ምርጥ ተጨዋቾች አንዷ በሆነችበት እና የዓመቱ የብሄራዊ የሴቶች እግር ኳስ ሊግ ምርጥ ተከላካይ በነበረችበት ዓመት ሳንዲያጎ ዌቭ የሊጉን ዋንጫ እንዲያሸንፍ ረድታለች።

በሽልማቱ የ39 ዓመታት ታሪክ ይህን ሽልማት ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ተከላካይ በመሆን ታሪክ የፃፈችው ናኦሚ ወደ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ በተቀላቀለችበት ሦስተኛ የውድድር ዓመት ላይ በርካታ የግል ክብሮች አሳክታለች።

ሽልማቱን አስመልክታ ሀሳብዋን ያጋራችው ኮከብ “ሽልማቱን ያሸነፈች የመጀመርያዋ ተከላካይ እና ሁለተኛ ጥቁር ተጫዋች በመሆኔ ክብርና ምስጋና ይሰማኛል፤ ይህ ግብ ጠባዊዎች፣ በኋላ መስመር እና በአጠቃላይ ቡድናችን ለሀገራችን ታሪካዊ ዓመት ለማስመዝገብ ያደረጉትን ጥረት ሁሉ የሚያረጋግጥ ነው” ብላለች። ከዚ በተጨማሪም በእግር ኳስ ህይወትዋ ትልቅ ድርሻ ለተወጡ ምስጋናዋን አቅርባለች። ” ሁልጊዜም ጓደኞቼን እና ቤተሰቦቼን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም በዚህ ጉዞ ውስጥ በእያንዳንዱ እርምጃ ከእኔ ጋር ነበሩ። አሰልጣኞቼ፣ የቡድን አጋሮቼ የክለብ እና የብሔራዊ ቡድን ጓደኞቼ ዛሬ የሆንኩትን ተጫዋች እንድሆን የረዱኝ ሰዎች ስለሆኑም ሁሉንም በጣም አመሰግናለሁ” ብላለች።