የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ የመልቀቂያ ደብዳቤን አስገብቷል

ሀዋሳ ከተማን በያዝነው የውድድር ዓመት የተቀላቀለው ተከላካይ በስምምነት ከክለቡ ጋር ሊለያይ ተቃርቧል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2016 የውድድር ዘመንን ለሀዋሳ ከተማ በመፈረም በሊጉ እየተጫወተ የሚገኘው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ሚሊዮን ሰለሞን ከክለቡ ጋር የልቀቁኝ ደብዳቤን ያስገባ ሲሆን ክለቡም ሊለቀው እንደሚችል ይፋ አድርጓል። የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ተጫዋች በ2015 ክረምት ወር ላይ አዳማ ከተማን በመልቀቅ ሀዋሳ ከተማን በአንድ ዓመት ውል እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ መቀላቀል የቻለ ሲሆን ያለፉትን አምስት ወራት በክለቡ ቆይታን ካደረገ በኋላ ግን የልቀቁኝ ደብዳቤን ስለ ማስገባቱ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።

እንደ ክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ኡቴሳ ኡጋሞ ገለፃ ከሆነ ተጫዋቹ የመልቀቂያ ደብዳቤውን አዳማ ክለቡ ባረፈበት ሆቴል በማስቀመጥ ለቡድን መሪው እንዲደርሰው መደረጉን ከጠቆሙ በኋላ ተጫዋቹ በደብዳቤው “በቤተሰብ ችግር ምክንያት እኔ የምፈልገውን እያሳካው ስላልሆነ በስምምነት እንለያይ” የሚል ሀሳቡን እንዳሰፈረ ለዝግጅት ክፍላችን አሳውቀዋል።

“ሪሴቭሽን አስቀምጫለሁ ብሎ ለቡድን መሪው ማመልከቻውን ሰጥቶታል፣ ስናነበው ‘በቤተሰብ ችግር ምክንያት እኔ የምፈልገውን እያሳካው ስላልሆነ በስምምነት ልቀቁኝ’ የሚል ደብዳቤ ነበር። ክለቡን እየጎዳም የቆየው እርሱ ነው፣ ትልቅ ደመወዝ ተካፋይም እርሱ ነው። እኛም ሳይመቸን ቆይቶ እርሱም ሳይመቸው ቆይቶ ከመጣ እንደ ፍላጎቱ ማስተናገድ ነው የሚል ሀሳብን ነው የያዝነው። ከእርሱ ጋር ሌላ የምንከራከርበት ሁኔታ የለም። ደብዳቤ ካስገባ ከቡድኑ ጋር ቀጥል ማለትም አይቻልም፣ በዚህ ላይ እርምጃን እንወስዳለን። በስምምነት ከእኛ ጋር እንዲላቀቅ ነው የምናደርገው።” ሲሉ ሥራ አስኪያጁ በምላሻቸው አሳውቀዋል።

የመልቀቂያ ደብዳቤውን ክለቡ ሀዋሳ የሚቀበል ከሆነ የተጫዋቹ ቀጣይ ማረፊያ ከዝውውር መከፈት ቀናቶች በኋላ እንደሚታወቅ ሰምተናል።