የሞሮኮ እና ኢትዮጵያን ጨዋታ ዩጋንዳዊያን ዳኞች ይመሩታል

ለዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ ነገ የሚደረገውን ወሳኝ መርሐ ግብር ዩጋንዳዊያን ዳኞች ይመሩታል።

ኮሎምቢያ ለምታስተናግደው የ2024 የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ውድድር ላይ አፍሪካን ለመወከል የመጨረሻ የደርሶ መልስ ጨዋታ በሞሮኮ እና በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ቡድኖች መካከል ይከናወናል። ቅዳሜ የሞሮኮ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አቻው ጋር ሞሮኮ አልጄጂዳ ከተማ በሚገኘው መሐመድ ኤል አብዲ ስታዲየም ምሽት 12፡00 ላይ የሚደርጉትን ጨዋታ የዩጋንዳ ዜግነት ያላቸው አራት ዳኞች ይመሩታል።

የዩጋንዳን ወንዶች ፕሪምየር ሊግን በብቃት የምትዳኘው እና ከወራቶች በፊት በአይቮሪኮስት ተሰናድቶ በነበረው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ በዳኝነት ተሳታፊ የነበረችው ዩጋንዳዊቷ የ32 ዓመት የመሐል ዳኛ ሻሚራ ናቫዳ በመሐል ዳኝነት ስትመራው የሀገሯ ዳኞች ኤልዛቤት ናሶሎ እና ጄን ሞቶኒ ረዳቶቿ ዲያና ሙሩንጊ በበኩሏ አራተኛ ዳኛ ሆና ታገለግላለች። በጨዋታ ታዛቢነት መርቫት ሁሴን ሳዲቅ ከሱዳን መመደባቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ እና የሞሮኮ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታ ከ8 ቀናቶች በኋላ ማለትም ጥር 12 በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚከናወን ሲሆን የደርሶ መልስ አሸናፊ መሆን የቻለው ቡድን አፍሪካን በመወከል ወደ ደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ኮሎምቢያ የሚጓዝ ይሆናል።