ሪፖርት | ፋሲል ከነማ ተከታታይ ድል ተቀዳጅቷል

ዐፄዎቹ በጌታነህ ከበደ ግሩም የቅጣት ምት ግብ ሠራተኞቹን 1ለ0 ረተዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ወልቂጤ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ሲገናኙ ወልቂጤ በወላይታ ድቻ ሽንፈት ከገጠመው ቡድኑ የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ በዛሬው ጨዋታው ሲያደርግ በሳሙኤል ዳንኤል ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ስንታየሁ መንግሥቱ ምትክ ወንድማገኝ ማዕረግ ፣ ዳንኤል መቀጫ እና አሜ መሐመድ ሲገቡ በፋሲሎች በኩል በአንፃሩ በድሬዳዋ ላይ ድል ያደረጉበትን ስብስብ ዛሬም ይዘው ገብተዋል።

09፡00 ላይ በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ፋሲሎች መጠነኛ ብልጫ ቢወስዱም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተደራጅቶ በመድረሱ በኩል ወልቂጤዎች የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም ግን በሁለቱም በኩል በርከት ያሉ የጠሩ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩም።

መሃል ሜዳ ላይ በተገደበው እንቅስቃሴ ሁለቱም ቡድኖች ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ፈታኝ ሆነው ለመቅረብ ሲቸገሩ የተሻለው የመጀመሪያ የጠራ የግብ ዕድልም 29ኛው ደቂቃ ላይ በዐፄዎቹ አማካኝነት ተፈጥሯል። ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ በረጅሙ ባሻገረው ኳስ ጌታነህ ከበደ በግንባር ገጭት ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሽመክት ጉግሣ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ኃይል በሌለው ሙከራ የግብ ዕድሉን አባክኖታል።

በፈጣን የመስመር አጥቂዎቻቸው ታግዘው አልፎ አልፎ ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ሠራተኞቹም 31ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። አቡበከር ሳኒ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል አምሣሉ ጥላሁንን በግሩም ክህሎት አታልሎ ለማለፍ ሲሞክር ተከላካዩ በሠራበት ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ጋዲሳ መብራቴ አሻምቶት ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ያገኘው አሜ መሐመድ ተገልብጦ ያደረገውን አስደናቂ ሙከራ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ በግሩም ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል ጌቱ ኃይለማርያም በቀኝ መስመር ባሻገረው እና አቡበከር ሳኒ በግንባር በገጨው ኳስ የተጋጣሚን ሳጥን መፈተን የጀመሩት ሠራተኞቹ 55ኛው ደቂቃ ላይም ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተው ሚኬል ሳማኬ የአሜ መሐመድን ጠንካራ ሙከራ አግዶበታል።

ካለፈው ጨዋታቸው በተለይም አማካይ ቦታ ላይ እጅግ ተዳክመው የቀረቡት ፋሲሎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማጠናከር ጥረት ቢያደርጉም 73ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከረጅም ርቀት ካደረገው ሙከራ ውጪ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረዋል።

በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ጨዋታው ተጋግሎ ሲቀጥል 84ኛው ደቂቃ ላይ ዐፄዎቹ ግብ አስቆጥረዋል። የወልቂጤው ግብ ጠባቂ ፋሪስ አለው ከሳጥን ውጪ ኳስ በመንካቱ የተሰጠውን የቅጣት ምት ምሕረት የለሹ አጥቂ ጌታነህ ከበደ እጅግ ድንቅ በሆነ ሁኔታ መትቶት የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ መረቡ ላይ አርፏል። የተሰጠው የቅጣት ምት ላይ ፋሪስ በእጁ ከመንካቱ በፊት ጥፋት ተሰርቷል በሚልም ወልቂጤዎች ተቃውሞ አስነስተዋል። ፋሲሎች 93ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ጌታነህ ከበደ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ያደረገውን ሙከራ ተከላካዮቹ ተረባርበው መልሰውበታል። ጨዋታውም በፋሲል ከነማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።