የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-1 ፋሲል ከነማ

ዐፄዎቹ በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ጎል ሠራተኞቹን 1ለ0 ከረቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት – ወልቂጤ ከተማ

ብርቱ ፉክክርን አድርገው ስለተሸነፉበት ጨዋታ…

“ጨዋታው ከመጀመሪያ ጀምሮ ጠንካራ ነው። የተጫወትነው ከፋሲል ጋር ስለሆነ ጥሩ ፉክክር አድርገናል እስከ 85ኛ ደቂቃ ድረስ ሄደናል ከዛ በኋላ ነው የተቆጠረብን እጅግ በጣም ጥሩ ነበር። ተጫዋቾቻችን እጅግ በጣም በጣም ጥሩ ነበሩ። ከአጨራረስ ውጪ ካልሆነ በቀር እጅግ በጣም ጥሩ ነበር ዛሬ ትልቅ መስዋዕትነት ነው የከፈሉት።”

በመጨረሻ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ጎልን እያስተናገዱ ስለ መገኘታቸው…

“ሽንፈቶች ሊኖሩ ይችላሉ ግን ሽንፈቶችን የምንቀበልባቸው መንገዶች ሊለያዩ ይችላሉ። ሰሞኑን የነበሩት የዛሬም አሁን ራሱን የቻለ ክፍተት ቢኖረውም ፣ ከዳኞች ጋርም በተያያዘ ትንሽ የሚታዩ ክፍተቶች ያሉ ይመስለኛል እኛ ከርቀት ስለሆንን ከቅርበት እነርሱ ስለሆኑ የሚያዩት ትንሽ ጥርጣሬዎች አሉ እንጂ 85 ደቂቃ ያው ጥፋቱ ከግብ ጠባቂ ጋር ያሉ ንክኪዎች ከመሆናቸው ሌላ የተለየ ነገር የለም ይሄን ከማለት ውጪ የተለየ ነገር የለም።”

መቀጠል አለበት የምትለው የቡድኑ የዛሬ ጠንካራ ጎን…

“ከበረኛ እስከ መጨረሻ ያሉት ጥሩ ናቸው ውጪም ያሉት ተቀይረው የሚገቡት የተሻሉ ናቸው። አሁንም ማሻሻል የምንፈልገው ግብ ማግባት ነው ፣ የተለየ ምንም ነገር የለም ቡድኑ ጥሩ ነው ማሻሻል ያለብን ጎል ማግባት ነው እርሱን ደግሞ ተነጋግረን ለመቀየር ነው የምንጥረው  እንጂ ልጆቼ እጅግ በጣም በጣም ጥሩ ስለነበሩ ደስተኛ ነኝ በዛሬው እንቅስቃሴ።”

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ድል ስላደረጉበት ጨዋታ…

“በጣም ፈታኝ ነበር ፣ ወልቂጤ በጣም ጥሩ ተፎካክረዋል ማለት ይቻላል። በእኛ በኩል በጠበቅነው ደረጃ ጨዋታውን ለመቆጣጠር አልቻልንም ፣ በጣም ብዙ ኳሶች ይቆራረጡ ነበር በተለይ ወደ ሦስተኛው ክፍል ከደረስን በኋላ ጥድፊያዎች ነበሩ ቶሎ ጨዋታውን ለማሸነፍ ካለን ጉጉት የተነሳ ቶሎ ቶሎ ኳሶች ይበላሹ ነበርና ያን ቦታ ተረጋግተን ዕድሎችን ለመፍጠር አልቻልንም ፣ በተለይ ከዕረፍት በፊት በሄድንባቸው መንገዶች ያገኘናቸው ኳሶች አሉ ግን ጥራት ወዳለው የጎል ሙከራ ለመቀየር አልቻልንም ነበር። ያ ትንሽ አዳጋች ነበር ዞሮ ዞሮ እንደዚህ አይነት ነገሮች ይኖራሉ የሚጠበቅ ነው በተለይ ከደረጃ በታች ካሉ ቡድኖች ጋር ስትጫወት የማሸነፍ ፍላጎት ፣ የመጫወት ፍላጎት በተነሳሽነትም ከፍተኛ ነገር እንደሚገጥመን ይታወቃል ግን መጨረሻ ጎል አግብተን ማሸነፍ ችለናል።”

ጌታነህ ከበደ ቢያስቆጥርም የአማካይ ክፍሉ የግብ ዕድል የመፍጠር ደረጃ በሚፈለገው ደረጃ ይገኛል ማለት ይቻላል…?

“እግር ኳስ አንድ ቀን እንደምትፈልገው ልትጫወት ትችላለህ ፣ አንድ ቀን ደግሞ ከዛ ልትወጣ ትችላለህ ፣ ብዙ ፋክተር አለው መጥፎ አልነበሩም ፣ ሲታገሉ እናያለን ግን ኳሶች በቀላሉ ነበር የሚበላሹት እነርሱን ለማስተካከል አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች መሥራት አለብን። በቁጥር የምናንስባቸው ፣ ረዳት የምናጣባቸው ሁኔታዎች አሉ እርሱ ላይ በደንብ መስራት እንዳለብን ይሰማኛል። በአጠቃላይ ግን አማካይ ላይ ብቻ ሳይሆን ወደፊት የሚሄደውም ኳስ ፊት መስመር ላይ ከደረሰ በኋላ ቶሎ ነው እኛ ጋር አይዘገይም እና እርሱን ማረም አለብን።”