ሪፖርት | ወላይታ ድቻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያለመሸነፍ ጉዞ ገቷል

እጅግ ማራኪ በነበረው የሣምንቱ ምርጥ ጨዋታ ወላይታ ድቻ በአዛርያስ አቤል ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 1ለ0 ረትቷል።

በሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ወላይታ ድቻ ከወልቂጤ ድላቸው ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ቅያሪ ዮናታን ኤልያስን አሳርፈው በዘላለም አባተ ሲተኩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው ከሀምበሪቾው ጨዋታ አንፃር የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥን አድርገዋል። እንዳለ ዮሐንስ ፣ አዲስ ግደይ እና አቤል ማሙሽ አርፈው ካሌብ አማንክዋ ፣ ሱለይማን ሀሚድ እና ሲሞን ፒተር ተተክተዋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ በኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ተደርጎበታል። ገና ጨዋታው በተጀመረበት የመጀመሪያ ደቂቃም ድቻዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ቢኒያም ፍቅሩ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አብነት ደምሴ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በንግድ ባንክ ተከላካይ ከመስመር ላይ ተመልሶበታል።

በመጀመሪያወቹ ደቂቃዎች በሙሉ ኃይላቸው ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ወላይታ ድቻዎች 22ኛው ደቂቃ ላይም ከረጅም ርቀት በቢኒያም ፍቅሩ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን አስወጥቶታል።

ቀስ በቀስ ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅተው ለመውጣት ጥረት ማድረግ የጀመሩት ንግድ ባንኮች በመጠኑ መነቃቃት ሲያሳዩ የመጀመሪያውን የጠራ የግብ ዕድላቸውን 24ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረዋል። ሲሞን ፒተር ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ኪቲካ ጅማ ያደረገውን ሙከራ የድቻ ተከላካዮች አግደውበታል።

በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን የመድረስ ፍላጎት እየታየበት በቀጠለው ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረው ዘላለም አባተ ከአበባየሁ ሀጂሶ በተቀበለው ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

ከወትሮው በተለየ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ተቀዛቅዘው የቀረቡት ንግድ ባንኮች ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥ የተሻለውን ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን አድርገዋል። ኪቲካ ጅማ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሱሌይማን ሐሚድ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች በጉዳት ምክንያት ወሳኝ አማካዮቻቸውን ለመቀየር ሲገደዱ በንግድ ባንክ በኩል ሀብታሙ ሸዋለም በብሩክ እንዳለ ምትክ በወላይታ ድቻ በኩል መሳይ ኒኮል በአብነት ደምሴ ምትክ ተቀይረው ገብተዋል።

እጅግ ተጋግሎ እና ለተመልካች እጅግ ማራኪ ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ አጋማሹ በተጀመረ በሴኮንዶች ውስጥ ንግድ ባንኮች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ሱሌይማን ሀሚድ ከመሃል በተሻገረለት ኳስ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

 

ጨዋታው 50ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ በጦና ንቦቹ አማካኝነት ግብ ተቆጥሮበታል። ፍጹም ግርማ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ሁለተኛ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታውን ያደረገው የመሃል ተከላካዩ አዛርያስ አቤል በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ተጭነው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ንግድ ባንኮች 55ኛው ደቂቃ ላይ ወሳኝ የግብ አጋጣሚ አግኝተው ኪቲካ ጅማ ከባሲሩ ኦማር በተሰነጠቀለት ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ አግዶበታል።

ዕረፍት የለሽ በሆነ እንቅስቃሴ ዐይን በማያስከድን እጅግ ብርቱ ፉክክር ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታ ንግድ ባንኮች 68ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ተቀይሮ የገባው ቢኒያም ጌታቸው ከኪቲካ ጅማ በተሻገረለት ኳስ ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በግሩም የጊዜ አጠባበቅ አቋርጦበታል።

እጅግ በተደራጀ እንቅስቃሴ ለተጋጣሚያቸው ክፍት ቦታዎችን በማሳጣት የተሳካ ጊዜን ያሳለፉት ወላይታ ድቻዎች 85ኛው ደቂቃ ላይም መሪነታቸውን ለማጠናከር እጅግ ተቃርበው ቢኒያም ፍቅሩ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ በአስደናቂ ሁኔታ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ብርቱ ፉክክር ተደርጎበት ጨዋታው በወላይታ ድቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በፕሪሚየር ሊጉ የእስካሁን ቆይታ ሳይሸነፍ የዘለቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ከአስር ጨዋታዎች በኋላ ያለመሸነፍ ጉዞው ተገቷል።