የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሽንፈት አስተናግዷል

በአሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ማጣርያ የመጀመሪያ ጨዋታውን በሞሮኮ አቻው ኤልጀዲዳ ላይ ሽንፈት አስተናግዷል።

በንፅፅር በተሻለ የተመልካች ቁጥር ታጅቦ በተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አውንታዊ ሆኖ ጨዋታውን የጀመረ ቢመስልም ግን ባለሜዳዎቹ ምሮኮዎች ቀዳሚ መሆን የቻሉት ገና በማለዳ ነበር። በ11ኛው ደቂቃ ያስሚን ዞሂር ሞሮኮን ቀዳሚ ያደረገችውን ግብ አስቆጥራለች።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የጨዋታውን የበላይነት ወስደው መጫወት የቻሉት ሞሮኮዎች በሂደት ግን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብልጫቸውን ቢያስረክቡም በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ላይ ግን አስፈሪ ነበሩ።

ሁለቱ ቡድኖች ከዕረፍት እንደተመለሱም ሞሮኮዎች በአምስት ደቂቃ ልዩነት ሁለተኛ ግባቸውን አግኝተዋል። አጥቂዋ ባሲር አምብሬ ደግሞ የግቧ ባለቤት ነበረች።

ከሁለተኛዋ ግብ መቆጠር በኋላ በነበሩት የጨዋታ ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተሻለ በተጋጣሚ የሜዳ ክልል ኳስን ለመቀባበል ቢሞክሩም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ከርቀት ከሚደረጉ ሙከራዎች እና ከማዕዘን ምት ከሚሻሙ ኳሶች ውጭ በቅብብል ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት እና አደጋ ለመፍጠር ሲቸገሩ ተመልክተናል።

ሞሮኮዎች በሁለተኛው አጋማሽ በርከት ያሉ ቁልፍ ተጫዋቾቻቸውን ቀይረው ያስወጡ ሲሆን በ71ኛው ደቂቃ የግብ ልዩነቱን ወደ ሦስት ሊያሰፉበት የሚችሉበትን አጋጣሚ ቢያገኙሞ ኤልኩሚር ካይና ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምንም እንኳን በተጠና መልኩ ባይሆን ወደ ሞሮኮዋ ግብ ጠባቂ ሱፊ ኢነየስ ተደጋጋሚ ኳሶችን መሞከር ቢችሉም የጨዋታው ውጤት ላይ ለውጥ ማስከተል ሳይችሉ ጨዋታው በሞሮኮው የ2-0 የበላይነት ተጠናቋል።

አፍሪካን በመወከል ወደ ኮሎምቢያ የሚያቀናውን ሀገር የሚለየው ወሳኙ የመጨረሻ ዘጠና ደቂቃ ጨዋታ የነገ ሳምንት ዕሁድ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።