የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ይጀመራል

በኮትዲቯር አዘጋጅነት የሚካሄደው 34ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ምሽት ይጀመራል።

ከጥር 13 እስከ የካቲት 11 የሚቆየው 34ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ አዘጋጅዋ ኮትዲቯር ከ ጊኒ ቢሳው ጋር ምሽት 05:00 ላይ በምታደርገው ጨዋታ ይጀመራል። አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘን ፈሰስ የተደረገበት ይህ ውድድር በአቢጃን፣ ቡዋኬ ፣ ኮርሆጎ፣ ሳን ፔድሮ እና ያሙሱኮሮ ከተሞች ላይ በተገነቡ ስታዲየሞች ይካሄዳል። ሀገሪቱ ውድድሩን ለማዘጋጀት አራት አዳዲስ ስታዲየሞችን ስትገነባ ሌሎች ሁለት ስቴድየሞችም እድሳታቸውን ጨርሰው የውድድሩን መጀመር በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ በርካታ ግምቶችም እየተሰጡ ይገኛሉ። ቁጥራዊ መረጃዎች በማቅረብ የሚታወቀው ኦፕታ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሞዴልን በመጠቀም ለሴኔጋል ቅድምያ የማሸነፍ ግምቱን ሲሰጥ የዓለም ዋንጫው ክስተት ሞሮኮ፤ የተትረፈረፈ የአጥቀዎች ክምችት ያላት ናይጄርያ፤ የሊቨርፑሉ ኮከብ ሞ ሳላህ የያዘችውና በውድድሩ ትልቅ ታሪክ ያላት ግብፅም ዋንጫውን የመውሰድ ትልቅ ግምት የተሰጣቸው ቡድኖች ሆነዋል። አዘጋጅዋ ኮትዴቭዋር፣ ካሜሩንና አልጄርያም ሌሌች ግምት የተሰጣቸው ሀገራት ሆነዋል። ለቀጣዩ አንድ ወር የትኩረት ማረፊያ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው አህጉራዊው ውድድር በእነዚህ ምድቦች የሚከናወን ይሆናል :-

ምድብ 1፡ ኮትዲቯዋር፣ ናይጄሪያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጊኒ-ቢሳው።

ምድብ 2፡ ግብፅ፣ ጋና፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ሞዛምቢክ

ምድብ 3፡ ሴኔጋል፣ ካሜሩን፣ ጊኒ፣ ጋምቢያ።

ምድብ 4፡ አልጄሪያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሞሪታኒያ፣ አንጎላ።

ምድብ 5፡ ቱኒዚያ፣ ማሊ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናሚቢያ።

ምድብ 6፡ ሞሮኮ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ዛምቢያ፣ ታንዛኒያ