ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ነቀምቴ ከተማ ከመሪዎቹ ጋር ያለውን ልዩነት መቀነስ የሚችልበትን ዕድል አምክኗል

በከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ሀ’ 12ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው ጅማ አባ ጅፋር እና ወልድያ ድል ሲቀናቸው ይርጋ ጨፌ ቡና እና ንብ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

ረፋድ 5:30 ላይ የተደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ሀ’ የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርን ከነቀምቴ ከተማ አገናኝቶ በጅማ አባ ጅፋር አሸናፊነት ተጠናቋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር በላቀ ሁኔታ ተሽለው የተገኙት ጅማ አባ ጅፋሮች ግብ ለማስቆጠር ተጭነው ተጫውተዋል። በአንፃሩ ነቀምቴ ከተማ ረጃጅም ኳሶችን በማዝወተር ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በ14ኛ ደቂቃ ጅማ አባ ጅፋር ኳስን መስርቶ ለመውጣት በሚሞክሩበት ጊዜ የነቀምቴ ከተማ የፊት መስመር ተጫዋች ኢብሳ ከልመንህ ታደሰ ኳስን በመንጠቅ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ነቀምቴዎች ይበልጥ ጫና በማሳደር ልዩነቱን ለማስፋት ተንቀሳቅሷል። በ36ኛው ደቂቃ የጅማ አባ ጅፋሩ ተጫዋች በሆነው ናትናኤል በርሄ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት ጌትነት ታፈሰ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ጅማ አባ ጅፋር የነቀምቴ ከተማን አለመረጋጋት ለመጠቀም እና ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርጓል። በ40ኛው ደቂቃ የጅማ አባ ጅፋሩ የመስመር ተከላካይ የሆነው ገለታ ኃይሉ ከጥልቀት በመነሳት ኳስን ይዞ ወደ ነቀምቴ ከተማ የግብ ክልል በመድረስ ከፊልሞን ገ/ፃድቅ ጋር ተቀባብሎ ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ አሚር አብዶ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ቀይሮት ቡድኑን መሪ አድርጓል። አጋማሹም በጅማ አባ ጅፋር መሪነት ተጠናቋል።

 

ሁለተኛው አጋማሽ ነቀምቴ ከተማ ግብ ለማስቆጠር በከፍተኛ ፍላጎት የተጫወቱ ሲሆን በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋር ኳስን በመያዝ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሲሞክር ተስተውሏል። በ57ኛው ደቂቃ የነቀምቴ ከተማ ተጫዋቹ ምኞት ማርቆስ ከርቀት አክርሮ በመምታት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቡ በኋላ ጅማ አባ ጅፋር በከፍተኛ ጫና ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ የነቀምቴን የግብ ክልል ሲፈትሹ ተስተውሏል። በ71ኛው ደቂቃ ጅማ አባ ጅፋር በጥሩ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ፊልሞን ገ/ፃድቅ ቡድኑን አሸናፊ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ነቀምቴ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ጅማ አባ ጅፋር ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት ጨዋታውን 3-2 በሆነ ውጤት ድል ማድረግ ችሏል።

7:30 የጀመረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡናን ከንብ አገናኝቶ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም የተቀዛቀዘ እና ብዙም ሳቢ ያልሆነ ጨዋታ ተመልክተናል። በአንጻራዊነት ንብ ኳስን ለመያዝ እና ወደ ግብ ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ በይርጋጨፌ በኩል የንብን ኳስ በማቋረጥ እና የሚያገኘውን ኳስ በመልሶ ማጥቃት የግብ እድል ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል። በ7ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ልማደኛው የፊት መስመር ተጫዋች ናትናኤል ሰለሞን በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ንብን መሪ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የቀዘቀዘ ጨዋታ እና የተቆራረጡ ኳሶችን አስመልክተውናል። አጋማሹም በንብ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ተሻሽሎ የገባው ይርጋ ጨፌ ቡና ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል። ንብ በአንጻሩ የወሰደውን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ሲጫወት ተስተውሏል። በ79ኛው ደቂቃ የይርጋ ጨፌ ቡና ተጫዋች የሆነው ሄኖክ ሞገስ በጨዋታ የተገኘችውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብ በመቀየር ቡድኑን አቻ አድርጓል።  ጨዋታውም 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

9:30 ላይ የተደረገው የዕለቱ የመጨረሻ ደቂቃ ወልዲያን ከሃላባ ከተማ አገናኝቶ ወልድያ ድል አድርጓል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ጥንቃቄ የበዛበት እና በሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ የተሞላበት ዓይነት አጨዋወት ተመልክተናል። ለዐይን ሳቢ ባልነበረው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥሩ ሀላባ ከተማ ተሽለው ተገኝተዋል። ወልዲያ ኳስን ለተጋጣሚው በመልቀቅ የሚገኙትን ስህተቶች ለመጠቀም ጥረት ሲያረጉ ተስተውሏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በ45ኛ ደቂቃ ወልድያ ከተማ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ኃይሌ ጌታቸው ከርቀት አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው ለመመለስ ምንም ዕድል በማይኖርበት ሁኔታ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። አጋማሹም በዚሁ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልዲያ የያዘውን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ሙሉ በሙሉ አፈግፍጎ የተጫወተ ሲሆን በአንጻሩ ሀላባ ከተማ በፊት መስመር ተጫዋቹ ፀጋ ከድር እና ከማል አቶም ተደጋጋሚ የግብ እድል ለመፍጠር ሲጥሩ ቢስተዋልም ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸዋል። ወልዲያም በተደጋጋሚ የጨዋታ ጊዜን ለመግደል ሲጥሩ ተስተውሏል። ጨዋታውም በወልዲያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።