ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ኤሌክትሪክ መሪነቱን ሲያሰፋ አዲስ አበባ ከተማ ያለመሸነፍ ጉዞው ተገቷል

በምድብ “ሀ” የ12ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ተደርገው ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ሲቀናቸው ሞጆ ከተማ እና ጅማ አባቡና ነጥብ ተጋርተዋል።

ረፋድ 3:30 ላይ የተደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡና በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ 1-0 ሽንፈት አስተናግዷል።

የመጀመሪያው አጋማሽ  ቤንች ማጂ ቡና ከዚህ ቀደም ከነበረው አቋም አንፃር ጥሩ የማይባል አቋም አሳይቷል። በአንፃሩ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ተነቃቅተው እና በሙሉ ፍላጎት ሲጫወቱ ተስተውሏል። ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጫና ሲፈጥሩ የነበሩት ኦሮሚያ ፖሊሶች በ14ኛው ደቂቃ ዳንኤል ዳርጌ ከጥልቀት በመነሳት የተጋጣሚ ተከላካዮችን በማታለል ግሩም ግብ አስቆጥሮ ቀዳሚ ሆነዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ የቤንች ማጂ ቡናን አለመረጋጋት እና የቅንጅት ችግር ተጠቅሞ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ  በድፍረት ተጭኖ ሲጫወት ተስተውሏል። ጨዋታውም በዚው ሁኔታ ቀጥሎ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛ አጋማሽ ቤንች ማጂ ቡና ተነቃቅተው ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ አጨዋወት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርጓል። ይህንንም ተከትሎ በ78ኛው ደቂቃ የቤንች ማጂ ቡናው ተጫዋች ዳግም በቀለ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ከመስመር ማዳን ችሏል። ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ  ያገኙትን የግብ ብልጫ ለማሽጠበቅ ከፍተኛ የሆነ ጥረት እና ጥሩ መከላከልን አሳይተውን ጨዋታውም በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ  1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በመቀጠል 5:30 ላይ በተደረገው መርሀግብር ሞጆ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ከጅማ አባ ቡና ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

ጥሩ እና ፈጣን እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ በ1ኛ ደቂቃ ጅማ አባቡና በጥቂት ቅብብል ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ ዘላለም አበበ ከርቀት አክርሮ መቶ የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላም ሞጆ ከተማ ደከም ያለ አጨዋወት አሳይቶናል። በአንፃሩ ጅማ አባቡና ተነቃቅተው ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ ተጫውቷል። አጋማሹም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድ በጅማ አባቡና መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ አሳይተውናል። በ52ኛው ደቂቃ ሞጆ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ጫና ለመፍጠር በሚጥርበት ሰአት ተነጥቀው ጅማ አባቡና በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ግብ በመድረስ እስጢፋኖስ ተማም የተከላካይ መስመሩን ጥሶ በመውጣት ግልፅ የግብ እድል አግኝቶ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት አጠናክሯል።  ሞጆ ከተማ ሁለት ግብ ካስተናገዱ በኋላ ወድያው በ55ኛው ደቂቃ ብሩክ ግርማ ኳስ ወደ ግብ ክልል ለመግባት ሲጥር በተሰራበት ጥፋት የተሰጠውን ቅጣት ምት መሳፍንት ነጋሽ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል። ሞጆ ከተማ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በከፍተኛ ፍላጎት ሲጫወት ተስተውሏል። በ69ኛው ደቂቃ በሞጆ ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው አቤኔዘር ታደሰ ተሻጋሪ ኳስን በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብ ቀይሮት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከአቻነቱ ግብ በኋላ ሞጆ ከተማ ጨዋታውን ለማቀዝቀዝ እና ነጥቡን ለማስጠበቅ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሲጫወት በአንፃሩ ጅማ አባቡና ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርግም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቆ ነጥብ ተጋርተዋል።

ቀን 7:30 ላይ የተደረገው ሦስተኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ የ2-1 ሽንፈት አስተናግዷል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ኮልፌ ክ/ከተማ በኳስ ቁጥጥር ተሽለው የተገኙ ሲሆን በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውሏል። በ11ኛው ደቂቃ አዲስ አበባ ከተማ በተመሳሳይ መንገድ ወደ ግብ በመድረስ የተገኘውን ግልፅ ኳስ አማኑኤል አሊሶ በፍፁም በራስ መተማመን አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የኮልፌ ክ/ከተማ የበላይነት በተስተዋለው ጨዋታ በ28ኛው ደቂቃ በአዲስ አበባ ከተማ በተሰራ ጥፋት ኮልፌ ክ/ከተማ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝቶ ሳሙኤል ወንድሙ አስቆጥሮ ክለቡን አቻ አድርጓል። አጋማሹም በአቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ኮልፌ ክ/ከተማ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተነቃቅተውና በከፍተኛ ፍላጎት ሲጫወቱ ተስተውሏል። በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማ የመቀዝቀዝ እና የቅንጅት ችግር ተስተውሎባቸዋል። በ50ኛው ደቂቃ ኮልፌ ክ/ከተማ ጫና በመፍጠር ያገኘውን የግብ እድል ዮናስ ወልዴ ብልጠት በተሞላበት መልኩ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ጨዋታው የቀዘቀዘበት እና ጥንቃቄ የበዛበት ጨዋታ ተደርጎ ምንም ግብ ሳይቆጠር በኮልፌ ክ/ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሰሞነኛ መነቃቃት ያሳየውና የደረጃው ግርጌ ላይ የነበረው ኮልፌ ክ/ከተማ ባስመዘገበው ጣፋጭ ድል ነጥቡን ከፍ ሲያደርግ አዲስ አበባ ከተማ የውድድር ዘመኑን የጀመርያ ሽንፈት አስተናግዷል።

የእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ 9:30 ላይ የተጀመረ ሲሆን በጨዋታው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስልጤ ወራቤን በሰፊ ነግብ ልዩነት በማሸነፍ ከተከታዮቹ መራቅ ችሏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ የበላይነቱን የወሰደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ16ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ያሬድ ብርሀኑ በግንባር የጨዋታውን የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል። ስልጤ ወራቤ ከግቡ መቆጠር በኋላ ፍፁም መረበሽ እና ፍላጎት ማነስ ሲስተዋልባቸው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቀላሉ የስልጤ ወራቤን የተከላካይ መስመር በመስበር የግብ እድል ፈጥሯል። በ34ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የፊት መስመር ተጫዋች አቤል ሀብታሙ ከያሬድ ብርሀኑ ጋር በድንቅ ቅብብል ይዞ የገባውን ኳስ ወደ ግብ ቀይሯል። ብዙም ሳይቆይ በ39ኛው ደቂቃ አቤል ሀብታሙ ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ያሬድ ብርሀኑ በቀላሉ በማስደገፍ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የበላይነት የቀጠለበት እና ስልጤ ወራቤ በተስፋ መቁረጥ እና በወረደ ፍላጎት አጋማሹን ጀምረዋል። በ49ኛው ደቂቃ አማኑኤል ብርሀኑ ከስልጤ ወራቤ የግብ ክልል ውጪ ያገኘውን ኳስ አክርሮ በመምታት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ግብ አስቆጥሯል። በቀሩት ደቂቃተዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ የጨዋታውን ፍጥነት በመቀነስ ኳስን በማንሸራሸር ቆይተዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አንዋር ሙራድ በድንቅ ክህሎት ተጫዋቾችን በማለፍ ግብ አስቆጥሮ የግብ መጠኑን ወደ አምስት ከፍ አድርጓል። ጨዋታውም በኢትዮ ኤሌክትሪክ 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተከታዩ በአምስት ነጥብ ርቆ ምድቡን መምራት ጀምሯል።