ኢትዮጵያዊው አልቢትር የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታን ዛሬ መዳኘት ይጀምራል

በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አልቢትር የሆነው ባምላክ ተሰማ ዛሬ የሚደረገውን የምድብ 6 ጨዋታ ይመራል።

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት በሚከናወነው የአህጉራችን ትልቁ የብሔራዊ ቡድኖች ውድድር ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባትሳተፍም በሦስት ባለሙያዎች መወከሏ አይዘነጋም። በዚህም በውድድሩ የቴክኒክ ጥናት ቡድን ውስጥ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ፣ በዳኝነት ባምላክ ተሰማ እንዲሁም በዳኞች ኮሚቴ አባልነት ደግሞ ኮሚሽነር ተስፋነሽ ወረታ በካፍ ተመርጠው ስፍራው ተገኝተው ግልጋሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

5ኛ ቀኑን ዛሬ ያስቆጠረው ውድድሩ ዛሬ የምድብ 6ኛ ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ በኢትዮጵያዊያን ሰዓት አቆጣጠር ምሽት 5 ሰዓት በላውረንት ፖኩ ስታዲየም የሚደረገውን የዲ አር ኮንጎ እና ዛምቢያ ጨዋታ ኢትዮጵያዊው አልቢትር ባምላክ ተሰማ በመሐል ዳኝነት እንደሚመራው ታውቋል።

ከባምላክ ጋር በመሆን ጂቡቲያዊው ሊባን አብዱልረዛቅ፣ የአዘጋጇ የሀገሬው ሰው ናሆ ኦታራ እንዲሁም ብሩንዲያዊው ንዳቢሃወኒማና ፓስፊክ በረዳትነት እና በ4ኛ ዳኝነት ተመድበዋል።