ሪፖርት | መቻል ተከታታይ ድል አሳክቷል

መቻል የሊጉ 8ኛ ድሉን ድሬዳዋ ከተማን 3ለ1 በማሸነፍ አስመዝግቧል።

ድሬዳዋ ከተማ ከተከታታይ ነጥብ መጣሎች በኋላ ባለፈው መድንን ድል ባደረገበት ጨዋታ ከተጠቀመው ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ጉዳት ገጥሟቸው በነበሩት አሰጋኸኝ ጴጥሮስ እና ቻርለስ ሙሴጌ ምትክ ዳግማዊ አባይ እና ካርሎስ ዳምጠውን በዛሬው ጨዋታ ሲጠቀሙ በተመሳሳይ ሀዋሳን አሸንፈው በመጡት መቻሎች በኩል በተደረገ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሳሙኤል ሳሊሶን በከነዓን ማርክነህ ፣ ምንይሉ ወንድሙን በአኩኔቶ ቺጂኦኪ ተክተው ቀርበዋል።

ጨዋታው ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ጅምሩን ቢያደርግም ሜዳ ላይ ይደረጉ ከነበሩ እንቅስቃሴዎች አኳያ በሙከራዎች ብዙም መድመቅ ያልቻለው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ የቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው ኳሱን አድርገው ለመንቀሳቀስ የጣሩት መቻሎች መሆን ቢችሉም ቡድኑ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በጥልቀት በሚደርስበት ወቅት የነበራቸው አፈፃፀም ደካማ ሆኖ ተንፀባርቋል። ለኋላ ክፍላቸው ሽፋን በመስጠት በአመዛኙ ከግራ እና ቀኝ ለመነሳት ይዳዱ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው ከተጋጣሚያቸው በንፅፅር ጎል ለማስቆጠር የተጓዙበት ርቀት ጥሩ ቢመስለም ከደቂቃ ደቂቃ ቡድኑ እየተዳከመ ሲሄድ ሜዳ ላይ አስተውለናል።

19ኛው ደቂቃ ላይ በቅብብል የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ጠርዝ ኤፍሬም አሻሞ አክርሮ መትቶ በላይኛው አግዳሚ ኳሷ ልትወጣ ችላለች። ከሙከራዎች አንፃር ቁጥብ ሆኖ በተወሰነ መልኩ ደግሞ አሰልቺ መልክን ተላብሶ የቀጠለው ጨዋታው መቻሎች ከመስመር በሚጣሉ ኳሶች መጠቀምን ከጀመሩ በኋላ ብልጫን ወደ መያዙ መጥተው በድግግሞሽ ተጋጣሚያቸውን የፈተኑ ሙከራዎችን ፈፅመዋል። 30ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ወደ ውስጥ ግርማ ዲሳሳ የላከለትን አኩኔቶ ቺጂኦኪ ጨርፏት ወደ ውጪ በግቡ ቋሚ ኳሷ ከወጣች ከአራት ደቂቃ ቆይታ መልስ መቻሎች ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል።

ግርማ ዲሳሳ ወደ ውስጥ አሻግሮ አቤል ነጋሽ ወደ ውስጥ የመለሳትን ኳስ ከነዓን ወደ ጎል መቶ ተከላካዩ እያሱ ለገሠ በእጅ መንካቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ከነዓን ማርክነህ ወደ ግብነት በቀላሉ ለውጧታል። በተጋጣሚያቸው ላይ የሚያደርጉትን ጥቃት በስልነት አጠናክረው የቀጠሉት መቻሎች 41ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎላቸውን ወደ ቋታቸው ከተዋል። አቤል በጥሩ ዕይታ ለአኩኔቶ ቺጂኦኪ ሰጥቶት አጥቂው ወደ ጎል መትቶ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ ሲተፋው አምበሉ በኃይሉ ግርማ አግኝቷት መረቡ ላይ ኳሷን አሳርፏታል። አጋማሹም በመቻል የ2ለ0 መሪነት ተገባዷል።

ከዕረፍት በመቀዛቀዝ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆኖ የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች የነበረባቸውን የመሐል ሜዳ ክፍተት ለማረም ያሬድ ታደሠን በአቤል አሰበ ለውጠው ቢመለሱም ቡድኑ ለመጫወት የፈለገውን የጨዋታ መንገድ ለመረዳት የተቸገርንበት ነበር። ጨዋታውን በሁለት ጎል መምራታቸው ተከትሎ መጠነኛ ሽፋንን ለተከላካይ መስመራቸው በመስጠት መንቀሳቀስ የቻሉት መቻሎች በንፅፅር በሽግግር ለመጫወት የሚጥሩበት ሂደት አመርቂ ነበር ማለት ያስችላል።

በአንፃራዊነት ከመጀመሪያው አጋማሽ የፉክክር መንፈሱ በእጅጉ ወርዶ የታየው የቡድኖቸ ጨዋታ የመጨረሻዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ቻርለስ ሙሴጌ እና ሱራፌል ጌታቸውን ድሬዳዋ ከተማዎች ለውጠው በማስገባት የአጥቂ ክፍላቸው ለማጠናከር ጥረት በማድረግ የጨዋታ መንገዳቸውን በተሻጋሪ ኳሶች ለመጫወት በታተሩበት ቅፅበት ጎል አስቆጥረዋል።

84ኛው ደቂቃ አቤል አሰበ ከቀኝ ወደ ውስጥ የላከለትን ኳስ ሱራፌል ጌታቸው አረጋግቶ ኳሷን  አንድ ተጫዋችን በማለፍ ከሳጥን ጠርዝ አክርሯ መቶ ድሬዳዋን ወደ ጨዋታ የምትመልስ ግብን ቢያስቆጥርም ከአንድ ደቂቃ በኋላ ግን ቡድኑ በተቃራኒው ሦስተኛ ጎልን አስተናግዷል። ከመሐል ሜዳ የተላከችን ኳስ የድሬዳዋ ተከላካዮች በተዘናጉበት ወቅት ኳሷን ለማስጣል ከራሱ የግብ ክልል ለቆ የወጣው ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ የሠራውን ስህተት ተከትሎ አፍትልኮ ወደ ጎል ያመራው እና የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን ያደረገው ወጣቱ አጥቂ ኢብራሂም መሐመድ ጎል አድርጎት በመጨረሻም ጨዋታው በመቻል 3ለ1 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል። ቡድኑም የዓመቱ 8ኛ ድሉን አሳክቶ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ መቀመጥ ችሏል።