የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-3 መቻል


“የራሳችን ስህተቶች ናቸው ዋጋ ያስከፈሉን” አሰልጣኝ አሥራት አባተ

“ጨዋታው በፈለግነው መንገድ ነው የሄደልን” አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ

ጦሩ ብርቱካናማዎቹን 3ለ1 ከረታበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ አሥራት አባተ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው ጠንካራ እንደሚሆን ገምተን ነበር። ጨዋታውን በጥንካሬ እያስቀጠልነው ነበር ያለነው። ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ ነው። ሆኖም እንደታየው ሦስቱም ጎሎች የጥንቃቄ ስህተቶች ናቸው አንደኛው ፔናሊቲ ነው። ልጁ እጁን ወደ የትም ማድረግ በማይችልበት ሁኔታ ላይ የተደረገ ነው። ሌሎቹም ሁለቱ ኳሶች የራሳችን የጥንቃቄ ስህተቶች ናቸው እና ጥሩ ፉክክር አድርገናል ብዬ አስባለሁ።”

ዛሬ ቡድንህ ላይ ያየኸው ጠንካራ እና ደካማ ጎን…?

“ጠንካራ ጎኑ ታክቲካሊ በጣም ጥሩ ነበርን። የራሳችን ስህተቶች ናቸው ዋጋ ያስከፈሉን እንጂ ታክቲካሊ ጥሩ ነን የጎል አጨራረሳችን እንደሚታየው በርካታ ዕድሎችን ነው ከጎል ሥር ሚስ የምናደርገው ያ ራሱን የቻለ ችግር ነው ብዬ አስባለሁ።”

ቡድኑ ላይ ያለው የተጫዋቾች ጉዳት ተጽዕኖ…?

“እንደ ቡድን እሱ ላይ ምክንያት ማድረግ አንችልም ግን ትልቁ ክፍተት ያለብን እሱ ነው። በተለይ አጥቂ ቦታ ላይ የተመስገን ፣ የቻርለስ ፣ ካርሎስ እና ኤፍሬም አብዛኞቹ በዚህ ደረጃ ነው ያሉት ያም ሆኖ ግን እስከ ችግሩ ጎል እያስቆጠርን ነው ያለነው። ነገር ግን ትናንሽ የሚባሉ የመከላከል ስህተቶቻችን ላይ ከነ ግብ ጠባቂ ጭምር ያ ዋጋ እያስከፈለን ነው። የተሻለ ደግሞ ቡድኑ በሙሉ ጤነኛነት ላይ ሲሆን አንድ ነገር ማግኘት እንደምችል ቡድኑ ያስታውቃል።”

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው በፈለግነው መንገድ ነው የሄደልን። ምክንያቱም እኛ ሁልጊዜም የራሳችንን ጨዋታ ብቻ ነው የምንመለከተው። ተፎካካሪያችን አዘውትረው የሚጠቀሙትን ነገር ነው አብዛኛው ይሄ ቡድን የሚጠቀመው ብለን ስለምናስብ እነዛን ነገሮች ዘግተን በራሳችን የጨዋታ መንገድ ሄደን በዛ መሠረት ጥሩ ተጫውተናል ብዬ አስባለሁ።”

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ስለተፈጠረባቸው ጫና…

“እግርኳስ እኮ ጎል ማስቆጠር ነው። ስለዚህ እኛ ጎል አስቆጥረናል እነሱ ቢጫኑንም ችግር የለውም። ምክንያቱም ጫናው ሁሉም ተጫዋች ወደኋላ በማፈግፈጉ የሚመጣ ነው። ጎል ስታገባ ሁሌም ተጫዋች ይሸሻል እና ከዛ አንጻር ነው።”

ስለ ወጣቱ ኢብራሂም መሐመድ…

“እምነት አለን በተጫዋቾቻችን ፤ በሁሉም ዕኩል ነው። የ17 ዓመት ልጅም የ30 ዓመትም ቢሆን ከእኔ ጋር ዕኩል ነው እና ሲገቡ አንድ ነገር እንደሚሠሩ እናውቃለን ምክንያቱም የተሻለ ቦታ ለማግኘት የተሻለ ጥረት ያደርጋሉ።”

ውጤታማ ጉዟችሁ ወደ ዋንጫ…?

“በፍጹም! አወዳዳሪው በስምንት ጨዋታ ዋንጫ የሚሰጠን ከሆነ አዎ! ከዛ ውጪ ግን አሁን ስለ ምንም ዋንጫ አናስብም ገና ነው። መጨረሻ ላይ ያለ ቡድን አንደኛ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ አለ እና እኛ ስለ ዋንጫ አይደለም ስለ ቀጣይ ጨዋታችን ነው የምናስበው። አሁን በቀጣይ ከፋሲል ጋር እንዴት ነው የምንጫወት የሚለው ነው ሀሳባችን።”