ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ኦሮሚያ ፖሊስ በግብ ተንበሽብሿል

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ‘ሀ’ 13ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው ኦሮሚያ ፖሊስ እና ቤንች ማጂ ቡና ድል ሲቀናቸው ጅማ አባ ቡና እና ስልጤ ወራቤ ነጥብ ተጋርተዋል።

ረፋድ 3:30 ላይ የተደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡና ይርጋጨፌ ቡናን ድል አድርጓል።

የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ ይርጋጨፌ ቡና ኳስን በመቆጣጠር ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። በአንፃሩ ቤንች ማጂ ቡና ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢጥርም ስኬታማ ኳሶችን ለመቀባበል ሲቸገር ተስተውሏል። ሆኖም ቤንች ማጂ ቡና በጨዋታው ራሱን በማስተካከል ውጤታማ ሆኗል። በ28ኛው ደቂቃ የቤንችማጂ ቡና ተጫዋች የሆነው ዘላለም በየነ ከይርጋጨፌ ግብ ጠባቂ ጋር በመገናኘት የተፈጠረውን ትልቅ የግብ ዕድል ያባከነበት አጋጣሚ ይታወሳል።

ሁለተኛው አጋማሽ ቤንች ማጂ ቡና የፊት መስመሩ ላይ ለውጥ በማድረግ ተጨማሪ የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በይርጋ ጨፌ በኩል እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ አጨዋወትን ተከትለዋል። በ52ኛው ደቂቃ ቤንች ማጂ ቡና ከመስመር የተላከውን ኳስ ሀሰን ሁሴን በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቀይሮታል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ቤንች ማጂ ቡና ጨዋታውን በመቆጣጠር ተጫውቷል። በ65ኛው ደቂቃ በድጋሚ ሀሰን ሁሴን ከግብ ክልል ራቅ ብሎ ያገኘውን ኳስ ከርቀት አስቆጥሮ የቡድኑን አሸናፊነት አረጋግጧል። ጨዋታውም በቤንች ማጂ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል 5:30 ላይ በተደረገው መርሀግብር ጅማ አባ ቡና እና ስልጤ ወራቤ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሚባል እና ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ አስመልክተውናል። ሆኖም ጥሩ የሚባል የግብ ዕድል አልተፈጠረም። የአጋማሹ መጠናቀቂያ አከባቢ ስልጤ ወራቤ በብሩክ ሰማ አማካኝነት ጥሩ የሚባል ጥረት ቢያደርግም ሳይቆጠር አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ቅያሪ ያደረጉት ጅማ አባ ቡናዎች የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ይህንን ተከትሎ ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ወደ ግብ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ስልጤ ወራቤም በመልሶ ማጥቃት የተወሰነ አጋጣሚ ያገኙ ቢሆንም ጨዋታው ምንም ግብ ሳያስተናግድ 0-0 ተጠናቋል።

ቀን 7:30 ላይ ነተደረገው ሦስተኛው ጨዋታ ኦሮሚያ ፖሊስ ሞጆ ከተማን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።

የጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ሞጆ ከተማ የተሻለ ሲሆን በመልሶ ማጥቃት ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በ22ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ዲጋሞ ከመስመር በመነሳት በራሱ ጥረት ጥሩ ግብ አስቆጥሮ ኦሮሚያ ፖሊስን መሪ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ሞጆ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ሲሆን በ31ኛው ደቂቃ ከመዕዘን ምት አከባቢ የተሻማውን ኳስ ኑራ ሀሰን በግንባር አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ብዙም ሳይቆይ በ33ኛው ደቂቃ ኦሮሚያ ፖሊስ በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ ክልል በመግባት ኃይሉ ዘመድኩን አስቆጥሮ ቡድኑን መልሶ መሪ አድርጓል። አጋማሹም 2-1 በሆነ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርዋወል።

ሁለተኛው አጋማሽ የኦሮሚያ ፖሊስ ሙሉ በሙሉ የበላይነት የታየበት አጋማሽ ሆኗል። በ51ኛው ደቂቃ ዳንኤል ዳርጌ በግሩም የቡድን ሥራ የተገኘውን ኳስ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት አጠናክሯል። ሞጆ ከተማ በረጃጅም ኳስ ተጠቅመው ወደ ግብ ለመድረስ ቢሞክሩም ውጤታማ መሆን ተስኗቸዋል። በዚሁ በመቀጠር በ61ኛው ደቂቃ በሞጆ ከተማ ተከላካይ ስህተት ያገኘውን ኳስ ቢቂላ ሲርቃ አስቆጥሯል። ጨዋታውም ቀጥሎ በ86ኛው ደቂቃ ዳንኤል ዳርጌ ከርቀት አስቆጥሮ ጨዋታው በኦሮሚያ ፖሊስ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የምድቡ የመጀመሪያ ዙር ማሳረጊያ የሆነው ተጠባቂው የአዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ነገ ማለዳ 03:00 ላይ ይከናወናል።