መረጃዎች | 49ኛ የጨዋታ ቀን

የሊጉ 12ኛ የጨዋታ ሳምንት መርሃግብር ነገ ፍፃሜውን ሲያገኝ የማሳረጊያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልክ ተጠናቅረዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ

9 ሰዓት ሲል ጅማሮውን በሚያደርገው በዚሁ መርሃግብር ኢትዮጵያ ቡናን ከወልቂጤ ከተማ የሚያገናኝ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ በሁሉም ውድድሮች ምንም ሽንፈትን ያላስተናገዱ ቢሆንም በመጨረሻ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ምንም እንኳን አቻ ቢለያዩም የነበራቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ግን ብዙም አመርቂ አልነበረም።

ብዙ ተጠብቆባቸው የውድድር ዘመኑን የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች አሁን ላይ በ16 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ከመሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወዲሁ በ13 ነጥቦች ይገኛሉ ፤ በመከለካከሉም ሆነ በማጥቃቱ አማካይ የሚባል አፈፃፀም ያለው ቡድኑ በሰንጠረዡ ከፍ ያሉ ቦታዎች ላይ ለመፎካከር በሁለቱም ረገድ አፈፃፀሙን ማሻሻል ይጠበቅበታል።

እጅግ አስቸጋሪ የሚባልን የውድድር ዘመን እያሳለፉ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ከመጨረሻ አራት የሊግ ጨዋታዎቻቸው አንድ ነጥብ ብቻን አሳክተው አሁን ላይ በዘጠኝ ነጥቦች አስራ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች የትኩረት ማዕከል ሆኖ የሰነበተው ቡድኑ በሊጉ በስድስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ያልቻሉ ሲሆን እስካሁን በሊጉ ያስቆጠሩት የግብ መጠን አምስት የመሆኑ ነገር እጅግ አሳሳቢው ጉዳይ ይመስላል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ብሩክ በየነ ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እና መሐመድኑር ናስር  በጉዳት ወልደአማኑኤል ጌቱ ደግሞ በቅጣት የነገው ጨዋታ ያልፋቸዋል ፤ በአንፃሩ በወልቂጤ በኩል ቅጣትም ጉዳትም የለም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ባደረጓቸው 6 ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና 5 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት ሲኖረው አንዱን አቻ ተለያይተዋል። ቡና 11፣ ወልቂጤ 6 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ይህንን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ከትዳር አጋሩ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ወጋየሁ ዘውዴ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እንዲሁም ከአራተኛ ዳኛው ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ጋር በጋራ ይመሩታል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከወላይታ ድቻ

የጨዋታ ሳምንቱ የማሳረጊያ መርሃግብር ሀዲያ ሆሳዕናን ከወላይታ ድቻ የሚያገናኝ ይሆናል።

በሊጉ በርከት ያሉ ጨዋታዎችን(7) በአቻ ውጤት መፈፀም የቻሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ካደረጓቸው አስራ አንድ ጨዋታዎች በስድስቱ ግብ ያለማስቆጠስራቸውን ጉዳይን ጨምረን ስንመለከት ቡድን ስለሚከተለው ጥንቃቄ መር አጨዋወት ዓይነተኛ ማሳያ ነው።

በውድድር ዘመኑ እኩል ሰባት ግቦችን ያስቆጠሩት እና የተቆጠረባቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች በተለይ ፊት መስመር ላይ ከዳዋ ሆቲሳ አለመኖር ጋር ተያይዞ የተገኙ ዕድሎችን ወደ ግብ የሚቀይር ሁነኛ ሰው ይፈልጋሉ።

በ17 ነጥቦች በሰንጠረዡ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ከተጋጣሚያቸው በተቃራኒ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ይበልጥ አዎንታዊነትን ጨምሮ የሚጫወት ቡድን እንደሆነ እየተመለከትን እንገኛለን።

ምንም እንኳን የወጥነት ችግር ብናስተውልባቸውም የአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹው ወላይታ ድቻ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴያየውን ወጥነት ባለው ውጤት ማጀብ ከቻሉ በሰንጠረዡ ከዚህ በተሻለ ስፍራ መገኘት በቻሉ ነበር።

በወላይታ ድቻዎች በኩል ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት መልካሙ ቦጋለ እና ባዬ ገዛኸኝ ውጭ ያለፈው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ያመለጠው አብነት ደምሴ ምንም እንኳን ከጉዳቱ ቢያገግምም በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አለየለትም።

ወጣቱ አልቢትር ኃይማኖት አዳነ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና አማን ሞላ ረዳቶቹ ቢንያም ወርቅአገኘሁ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆነው ይህን የጨዋታ ሳምንቱን ማሳረጊያ መርሃግብር የሚመሩ ይሆናል።