ሪፖርት | ሀምበርቾ በፕሪምየር ሊግ ታሪክ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል

በምሽቱ መርሐግብር ሲዳማ ቡናን የገጠሙት ሀምበርቾዎች በበረከት ወንድሙ ግቦች 2-0 በማሸነፍ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን አሳክተዋል።

በምሽቱ መርሐግብር ሲዳማ ቡና እና ሀምበርቾ ሲገናኙ ሲዳማዎች በ11ኛው ሣምንት ባህር ዳር ከተማን 2ለ0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ጽዮን ተስፋዬ ፣ ብርሃኑ በቀለ ፣ ሙሉቀን አዲሱ ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ቡልቻ ሹራ በጊት ጋትኮች ፣ ደስታ ደሙ ፣ አቤኔዘር አስፋው ፣ እንዳለ ከበደ እና ዳመነ ደምሴ ተተክተው ገብተዋል። በተመሣሣይ ሣምንት በሻሸመኔ ከተማ 3ለ0 የተረቱት ሀምበርቾዎች በአንጻሩ የሰባት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ትዕግሥቱ አበራ ፣ ዲንክ ኪያር ፣ አብዱልሰላም የሱፍ እና አቤል ከበደ ብቻ ካለፈው ጨዋታ የቀጠሉ ቋሚ ተሰላፊዎች ሆነዋል።

12፡00 ሲል በዋና ዳኝነት የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታውን በመራው መስፍን ዳኘ ፊሽካ አማካኝነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማዎች በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነት መውሰድ ችለው 13ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን ሙከራቸውን ሲያደርጉ ይገዙ ቦጋለ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ ሲይዝበት ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ብርሃኑ በቀለ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ቡልቻ ሹራ ተጨማሪ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ቢያደርግም ለግብ ጠባቂው ፈታኝ አልነበረም።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ይወሰድባቸው እንጂ በአቤል ከበደ ጥሩ አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ከቀሩ በኋላ የአጋማሹን የተሻለ ንጹህ የግብ ዕድል የፈጠሩት ሀምበርቾዎች 25ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ወርቃማ አጋጣሚ አግኝተው ማናየ ፋንቱ ከመሃል ሜዳ ከአፍቅሮት ሰለሞን በተሰነጠቀለት ኳስ ከግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ ጋር ቢገናኝም ኳሱን ሙሉ በሙሉ በእግሩ ሳያገኘው ቀርቶ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቶበታል።

ሲዳማ ቡናዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር እየበዙ ቢደርሱም እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲቸገሩ አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ ቡልቻ ሹራ ከሳጥን አጠገብ በደረቱ አብርዶ ዓየር ላይ እንዳለ በመምታት ያደረገው በግቡ አግዳሚ በኩል የወጣ ሙከራም የተሻለው ሙከራቸው ነበር።

ከዕረፍት መልስ አስደናቂ አጀማመር ያደረጉት ሀምበርቾዎች 48ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አፍቅሮት ሰለሞን ያመቻቸለትን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመግባት የተቆጣጠረው በረከት ወንድሙ በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ ሀምበርቾዎች 60ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረው በረከት ወንድሙ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ ከመለሰው በኋላ ኳሱን ያገኘው አፍቅሮት ሠለሞን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ተቀዛቅዘው የቀረቡት ሲዳማዎች ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት ሲቸገሩ 62ኛው ደቂቃ ላይ ብርሃኑ በቀለ ከረጅም ርቀት አክርሮ መትቶት ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ ከያዘው ሙከራ ውጪም የተጋጣሚን ሳጥን መፈተን አልቻሉም።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ማስቀጠል የቻሉት ሀምበርቾዎች 72ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አላዛር አድማሱ ከረጅም ርቀት ያደረገውን አስደናቂ ሙከራ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ አስወጥቶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ሁለቱም ቡድኖች ብርቱ ፉክክር ቢያደርጉም ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 6 ደቂቃዎች ውስጥ የመጨረሻው ደቂቃ ላይ ሀምበርቾዎች ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው ዳግም በቀለ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል እየገፋ ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው ያገኘው በረከት ወንድሙ በቀላሉ አስቆጥሮት ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል። ጨዋታውም በሀምበርቾ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉም ለሀምበርቾ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከጨዋታዉ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የግብ ዕድሎችን አለመጠቀማቸው እና ጥሩ ያልነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው ለሽንፈት እንደዳረጋቸው ሲገልጹ ያደረጉት የተጫዋቾች ቅያሪ ስኬታማ እንዳልነበር እና ሁሉም ተጫዋቾች ላይ ያዩት የማጥቃት እንቅስቃሴ ደካማ እንደነበር ጠቁመዋል። የሀምበርቾው አሰልጣኝ መላኩ ከበደ በበኩላቸው ድሉ በራስ መተማመናቸውን ለመመለስ እንደሚረዳቸው ጠቅሰው ስለ ቀጣዩ ጨዋታ እንደሚያስቡ እና የውድድር ጊዜው ገና መሆኑን ጠቁመው የበረከት ወንድሙን ብቃትም አድንቀዋል።