ሪፖርት | ቡናማዎቹ ከተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል

ኢትዮጵያ ቡና በአንተነህ ተፈራ ብቸኛ ጎል ወልቂጤ ከተማን 1ለ0 በመርታት የውድድር ዘመኑ አምስተኛ ድሉን አግኝቷል።

በአስራ አንደኛ ሳምንት መርሀግብር ሁለቱም ቡድኖች ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር 1ለ1 ከተለያዩበት ጨዋታቸው አኳያ በተመሳሳይ የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገዋል። ኢትዮጵያ ቡና ሃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ አስራት ቱንጆ እና መሀመድ ኑርናስር አርፈው ራምኬል ጀምስ ፣ ኤርሚያስ ሹምበዛ እና አንተነህ ተፈራ ሲተኩ በወልቂጤ በኩል ደግሞ ሔኖክ ኢሳያስን በአዳነ በላይነህ ፣ ወንድማገኝ ማዕረግን በተስፋዬ መላኩ እና አሜ መሐመድን በስንታየሁ መንግስቱ ያደረጓቸው ለውጦቻቸው ናቸው።

ከረር ካለው የአዳማ ፀሀይ ጋር ታጅቦ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ኖሯቸው ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ሳይቸገሩ በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ላይ መድረስ ቢችሉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል አጠቃቀማቸው ግን በእጅጉ ደካማ ነበር። የአማካይ ቁጥራቸውን አምስት በማድረግ በይበልጥ የበላይነት በመውሰድ የፈጣን አጥቂዎቻቸውን ጉልበት ለመጠቀም መንቀሳቀሳቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች መስፍን እና አብዱልከሪም ባደረጓቸው የሳጥን ውጪ ቀዝቀዝ ያሉ ሙከራዎችን በመጀመሪዎቹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ አድርገዋል።

ወደ ቀኝ የሜዳው ክፍል አጋድለው መጫወትን የመረጡት ወልቂጤ ከተማዎች በበኩላቸው በጋዲሳ እና ጌቱ አማካኝነት በጥልቀትም ሆነ በተሻጋሪ አልያም ደግሞ በሚገኙ የቆሙ ኳሶች መነሻነት በመጠኑም ቢሆንም ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ባደረጉበት ሂደት ጥሩ ዕድልን ፈጥረዋል። 11ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ወደ ግብ ክልል የተላከን ኳስ ዳንኤል መቀጮ እና መሳይ ፓውሎስ በንክኪ ያደረሱትን ኳስ ተስፋዬ መላኩ አግኝቶ ቢመታውም የግቡን ቋሚ ታካ ኳሷ ወደ ውጪ ወጥታለች። ወልቂጤ ከተማዎች ለማጥቃት ወደፊት በሚሄዱበት ወቅት ፈጠን ያሉ ሽግግሮችን ወደ መጠቀሙ የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል።

33ኛው ደቂቃ በፍጥነት ወደ ቀኝ ቦታ ጌቱ ሀይለማርያም ለማጥቃት መሄዱን ተከትሎ ነፃ ቦታውን ያገኘው መስፍን ታፈሰ ኳስን ገፋ አድርጎ በግራ እግሩ ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት የላከለትን ኳስ አንተነህ ተፈራ ወደ ግብነት ለውጧት ቡድኑ ቀዳሚ አድርጓል። ጎልን ካስተናገዱ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ቶሎ ቶሎ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረትን ያደረጉት ሠራተኞቹ 37ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ የጨዋታ ሂደት ጋዲሳ የጣለለትን ስንታየሁ በግንባር ገጭቶ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰችበት ምንአልባትም ቡድኑን ወደ አቻነት የምታሸጋግር ዕድል ሆና አጋማሹ በቀሪዎቹ ምንም ሳያስመለክተን ወደ መልበሻ ክፍል በ1ለ0 የቡናማዎቹ መሪነት ተገባዷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ የፉክክር መንፈሱ ተመጣጣኝ ይዘትን ቢይዝም በሙከራዎች ረገድ ግን ወልቂጤ ሻል ያለ ቆይታ ነበረው። አጋማሹ እንደተጀመረ መስፍን ታፈሰ አከታትሎ ሁለት ኢላማቸውን መጠበቅ ያልቻሉ ሙከራዎች በኢትዮጵያ ቡና በኩል ካደረገ በኋላ በተለይ ከቆመ እና ከሁለቱ ኮሪደሮች በሚነሱ ተንጠልጣይ ኳሶች ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ በብርቱ መታገልን የጀመሩት በጊዜ ነበር። 49ኛው ደቂቃ አዳነ ከግራ የተገኘን ቅጣት ምት በረጅሙ ወደ ግብ ሲያሻማ ተስፋዬ በግንባር ገጭቶ የግቡ ቋሚ ብረት ኳሷን ከጎልነት አግዷታል።

ቅብብሎች ከወጥነት ይልቅ መቆራረጦች ከደቂቃ ደቂቃ በበዙበት የቡድኖቹ ጨዋታ 59ኛው ደቂቃ ወልቂጤ ስንታየሁ እና መድንን በፉዓድ አብደላ ተመስገን በጅሮንድ በመተካት ተሻጋሪ ኳስን አልያም የተመስገንን የቀኝ ክፍል መጠቀም ላይ በይበልጥ ትኩረት ካደረጉ በኋላ በድግግሞሽ ሙከራዎችን አድርገዋል። ተመስገን በጅሮንድ ከቀኝ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ መቶ በረከት የያዘበት እና ጋዲሳ ወደ ሳጥን ከተከላካይ ጀርባ ጥሎ ተመስገን በግንባር ገጭቶ ኳሷ መረብ ላይ አረፈች ሲባል ወደ ውጪ የወጣችበት አጋጣሚ ተጠቃሾቹ ናቸው።

የመስፍን ታፈሰን ግልጋሎት የመጨረሻዎቹን ሀያ ደቂቃዎች በደንብ ሲጠቀሙ የተስተዋሉት ቡናማዎቹ የሚገኙ ዕድሎቻቸው ከጥራት አንፃር የተዳከመ መልክ ነበረው ማለት ይቻላል። መስፍን ከርቀት ያደረጋት እና 69ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ከቀኝ መነሻውን አድርጎ ለኤርሚያስ ሰጥቶት አማካዩ ያመቻቸውን አብዱልከሪም በቀጥታ መቶ በግቡ አግዳሚ ኳሷ ወደ ወጥታለች። ወልቂጤ ከተማ ወደ አቻነት ለመምጣት በመጨረሻዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ጫናን ሲፈጥሩ ይታይ እንጂ የቡድኑ የአጨራረስ ውስንነት ዋጋ አስከፍሎት ጥንቃቄ ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴ መርጠው የተጫወቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከተከታታይ ሁለት ጨዋታ ነጥብ መጣሎች መልስ 1ለ0 አሸንፈው ወጥተዋል።

ከጨዋታው መቋጫ በኋላ የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ጨዋታው ጥሩ መሆኑን ገልፀው በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድናቸው መቀዛቀዝ እንደነበረው ገልፀው በሁለተኛው ግን የምንችለው አድርገን ጥሩ ተጫውተን ጥሩም ነበርን ፤ የተገኙ ዕድሎችን ያለ መጠቀም የአጨራረስ ችግር መኖሩን ተናግረዋል በቀጣይም ተደጋጋሚ ስራዎች እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ጨዋታውን ባሰብነው ልክ አላገኘነውም ካሉ በኋላ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ብዙም ዕድሎች አልፈጠርንም ብለው ከተናገሩ በኋላ የተገኘውን አጋጣሚ ተጠቅመው ማግባታቸውን ጠቁመው ቡድናቸው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን አቻ ስለወጣ ጭንቀት እንደነበር የተከፈቱ የተጋጣሚ ቦታዎችን ለመጠቀም አልመው ያንንም መጠቀማቸውን በንግግራቸው ጠቁመዋል።