የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ12ኛ ሣምንት ምርጥ 11

የአሥራ ሁለተኛ ሣምንት ጨዋታዎችን መነሻ በማድረግ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አደራደር ፡ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ምንታምር መለሰ – ሀምበርቾ

ብዙም የቋሚነት ዕድል ያላገኘው እና ባሳለፍነው ሣምንት አራተኛ ጨዋታውን ያደረገው ግብ ጠባቂው ምንታምር ቡድኑ ሲዳማን 2ለ0 በመርታት በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ የመጀመሪውን ድል ሲያሳካ ከመለሳቸው ስድስት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ባሻገር የኋላ መስመሩ ላይ በራስ መተማመን በመጨመር እና የጨዋታውን ግለት በሚፈልጉት ሂደት ያስቀጠለበት መንገድ ተመራጭ አድርጎታል።

ተከላካዮች

ዳግማዊ አባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ለዓመታት ከከፍተኛ ሊግ የእግርኳስ ቆይታው በኋላ ዘንድሮ ወደ ሊጉ ብቅ በማለት እራሱን እየፈለገ የሚገኘው ዳግማዊ የአሰጋኸኝ ጴጥሮስን መጎዳት ተከትሎ በቋሚ አሰላለፍ ተካትቶ በወሳኙ ጨዋታ ሦስት ነጥብን ቡድኑ እንዲያገኝ ከቡድን አጋሮቹ ጋር የሚቻለውን አድርጓል። ዳግማዊ ሜዳ ላይ ጥሩ ቆይታ የነበረው ሲሆን በማጥቃት እና በወጥነት በመከላከልም ለቡድኑ ድል ያበረከተው ሚና ቀላል አልነበረም።

ምንተስኖት ከበደ – ሻሸመኔ ከተማ

በተከታታይ ሣምንታት እጅግ ብርቱ የሆነ የመከላከል ብቃት እያሳየ የሚገኘው ምንተስኖት ባሳለፍነው ሣምንት ቡድኑ ከመድን ጋር ነጥብ ሲጋራ አደገኛ ኳሶችን በአንድ ንክኪ ሲያቋርጥበት የነበረው መንገድ እና የኋላ መስመሩ ላይ የፈጠረው በራስ መተማመን በምርጥ ቡድናችን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

ስቴፈን ባዱ አኖርኬ – መቻል

ለሊጉ እንግዳ የሆነው ስቴፈን ባዱ ከአስቻለው ታመነ ጋር ጥሩ የመከላከል ጥምረት በማሳየት እራሱን እያስተዋወቀ ይገኛል። መቻል ከ 76 ደቂቃዎች በላይ በተጫዋች ቁጥር ብልጫ ተወስዶበት ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ሲጋራም የተጋጣሚን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመመከቱ በኩል የመሃል ተከላካዩ አስተዋጽኦ የጎላ ነበር።

አብዱለጢፍ መሐመድ – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከተማ ከአሰልጣኝ ስንብት በኋላ ወሳኝ ድል ባስመዘገበት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ የግራ መስመር ተከላካዩ ሚና ላቅ ያለ ነበር። ከተሰጠው የመከላከል ሚና በተጨማሪ በማጥቃቱ የተዋጣለት ተጫዋቹ ለመጀመሪያዋ የኤፍሬም አሻሞ ጎል በማቀበሉ እና በተደጋጋሚ የፈጠራቸውን የግብ ዕድሎች መነሻ በማድረግ በስብስባችን አካተነዋል።

አማካዮች

መስዑድ መሐመድ – አዳማ ከተማ

አዳማ ከተማ ከድል ረሃቡ ጋር በታረቀበት የአሥራ ሁለተኛ ሣምንት ጨዋታ ወቅት የባለ ብዙ ልምዱ አማካይ መስዑድ መሐመድ አስተዋፆኦ ከፍተኛ ነበር። ተጫዋቹ በሜዳ ላይ የቡድኑን ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማሳለጡ በኩል የነበረው ሚና ጥሩ ከመሆኑ ባሻገር ለወጣት ተጫዋች ያካፈለውን ልምድ እና እርጋታ ስንመለከት በምርጥ አሥራ አንድ ውስጥ ሊካተት ችሏል።

አብነት ደምሴ – ወላይታ ድቻ

ወላይታ ድቻ ከሀድያ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ሲወጣ ግዙፉ የመሐል ሜዳ ተጫዋች ቡድኑን ከሽንፈት ለመታደግ ያደርግ የነበረው ተጋድሎ ቀላል የማይባል ነበር። መሐል ሜዳው ላይ ቡድኑ ብልጫ እንዳይወሰድበት የተሰጠውን ሚና በአግባቡ ሲወጣ የታየው ተጫዋቹ የቡድኑን ብቸኛ ግብም በግሩም ሁኔታ ከቅጣት ምት ማስቆጠሩን ተከትሎ በምርጫችን ሊካተት ችሏል።

አቤል አሰበ – ድሬዳዋ ከተማ

ወጣቱ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ጥሩ የጨዋታ ሣምንትን አሳልፏል። መሃል ሜዳ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ብልጫ እንዳይወሰድ ሲያደርግ የነበረበት እና ለሁለተኛዋ ጎልም መገኘት ትልቁን ድርሻ መወጣቱ በሣምንቱ ስብስባችን ውስጥ ልናካተው ችለናል።

 

አጥቂዎች

በረከት ወንድሙ – ሀምበርቾ

ሀምበሪቾ በታሪክ የመጀመርያውን ወሳኝ ሦስት ነጥብ ሲያሳካ የወጣት አጥቂው በረከት ወንድሙ ድርሻ የጎላ ነበር። ፈጣን እና ራሱን ነፃ አድርጎ ጎሎችን ለማስቆጠር ያደርግ የነበረው ጥረት ለሲዳማ ቡና ተከላካዮች ከፍተኛ ስጋት ሆኖ አልፏል። ለመጀመርያ ጊዜ ስሙን በሊጉ ጎል አስቆጣሪዎች ስም ዝርዝር ውስጥ በማስገባት ራሱን ያስተዋወቀበትን ሁለት ወሳኝ ጎሎችን በማስቆጠር ቡድኑን ባለ ድል እንዲሆን በማስቻሉ በቦታው ከቦና ዓሊ ጋር ተፎካክሮ ምርጫ ውስጥ መካተት ችሏል።

አዲስ ግደይ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

አዲስ ግደይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በተቀላቀለበት ገና በመጀመርያው ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ጊዜ ለራሱም ለቡድኑም አስደሳች እንደሆነ እሙን ነው። ንግድ ባንክ ባህር ዳርን በመርታት ሊጉን በቀዳሚነት እንዲመራ በማስቻሉ ረገድ የመስመር አጥቂው ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ልዩ ነበር። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ራሱን ነፃ አድርጎ ለመግባት ያልተቸገረው እና በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅትም ስኬታማ የነበረው አዲስ ከፈጠራቸው የግብ ዕድሎች ባሻገር የቡድኑን የማሸነፊያ ወሳኝ ጎል በማስቆጠር ያሳየው ስኬት ምርጫ ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።

ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ

ወጣቱ አጥቂ ዮሴፍ ታረቀኝ አዳማ ከተማ ሀዋሳ ከተማን 3ለ2 በመርታት ከድል ጋር እንዲታረቅ በማስቻል በኩል ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር የነበረው ድርሻ በግልፅ የሚታይ ነበር። ዮሴፍ አንድ ጎል በጨዋታ እንቅስቃሴ አንዱን ከቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ማስቆጠር ሲችል ከሁለቱ ጎሎች በተጨማሪ ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን የሀዋሳ ከተማን የመከላከል አጥርን ሲያፈራርስ የነበረበት እንቅስቃሴ ስብስባችን ውስጥ እንዲገባ አስችሎታል።

አሰልጣኝ መላኩ ከበደ – ሀምበርቾ

አሰልጣኝ መላኩ ሀምበርቾን በጊዜያዊነት ከተረከቡ ወዲህ ቡድኑ በአንጻራዊነት መሻሻል እየታየበት እንደሚገኝ የባለፉት ጨዋታዎች ምስክሮች ናቸው። በተለይ ሲዳማ ቡናን በመርታት ቡድኑ በፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት ነጥብ ሲያሳካ አሰልጣኝ መላኩ ቡድኑ ከተደጋጋሚ ሽንፈት እንዲወጣ በስነ ልቦናው በማዘጋጀት የሠሩት ሥራ ፣ የሲዳማን እንቅስቃሴ በማቋረጥ እና በራሳቸው የጨዋታ መንገድ የተጫዋቾችን አጠቃቀም በመቀያየር ያደረጉት ለውጥ ለድሉ ከፍተኛ ሚና የነበረው በመሆኑ ከአሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ ጋር ተፎካክረው ምርጥ አሥራ አንድ ቡድናችንን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ ተመርጠዋል።

ተጠባባቂዎች

ቢኒያም ገነቱ – ወላይታ ድቻ
እስማኤል አብዱልጋኒዩ – ድሬዳዋ ከተማ
ወንድሜነህ ደረጄ – ኢትዮጵያ ቡና
በረከት ወልደዮሐንስ – ሀዲያ ሆሳዕና
በረከት ግዛው – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ቦና ዓሊ – አዳማ ከተማ
መስፍን ታፈሰ – ኢትዮጵያ ቡና
አንተነህ ተፈራ – ኢትዮጵያ ቡና