ሪፖርት | የጦና ንቦቹ ደረጃቸውን ያሻሻሉበት ድል አስመዘገቡ

የቢንያም ፍቅሬ ብቸኛ ግብ የጦና ንቦቹን ሦስት ነጥብ አስጨብጣለች።

ወላይታ ድቻዎች ባለፈው ሳምንት ከሆሳዕና ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ አዛርያስ አቤል፣ ፀጋዬ ብርሀኑ፣ ኬኔዲ ከበደና ናታን ጋሻውን በአንተነህ ጉግሳ፣ አናጋው ባደግ፣ እዮብ ተስፋዬና ባዬ ገዛኸኝ ተክተው ሲገቡ ሀምበሪቾዎች በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ከተቀዳጀው ስብስብ ተመስገን አሰፋን በንጋቱ ጎዶቤ ቀይረው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ሁለት የተለያየ አቀራረብ ያላቸውን ክለቦች ባገናኘው ጨዋታ የጦና ንቦቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው በርካታ የግብ ዕድሎች ሲፈጥሩ ሀምበሪቾዎች በበኩላቸው ወደ ሳጥኑ ይበልጥ በተጠጋ አቀራረብ በመልሶ ማጥቃቶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ከአጋማሹ የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጀምሮ ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ወላይታ ድቻዎች በርካታ የግብ ዕድሎች መፍጠር ቢችሉም በአጥቂዎቹ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ምክንያት ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም፤ ሆኖም በባዬ ገዛኸኝና አብነት ደምሴ አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል።

በተለይም ባዬ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር የተሻገረችለትን ኳስ ጨርፎ ያደረጋት ሙከራ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀው ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሲቀሩትም ጥረታቸው ሰምሮ ጨዋታውን መምራት ችለዋል፤ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ቢንያም ፍቅሩ ከአማካዩ ዘላለም አባቴ የተሻገረችለትን ኳስ አስቆጥሮ የጦና ንቦቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

በአጋማሹ ወደ ሳጥናቸው በተጠጋ አደራደር ለመከላከልና በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ሀምበሪቾዎች በርከት ያሉ የጠሩ የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም፤ ሆኖም በማናዬ ፋንቱና አፍቅሮት ሰለሞን አማካኝነት ከረዥም ርቀት ሙከራዎች አድርገዋል። አላዛር አድማሱ ከአፍቅሮት ሰለሞን የተሻገረችለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራም ቡድኑ ካደረጋቸው ሙከራዎች በተሻለ ለግብ የቀረበች ነበረች።

ቢንያም ፍቅሩ በጥሩ መንገድ ወዳ ሳጥኑ ይዟት ገብቶ በመታትና ምንታምር መለስ በሚያስደንቅ ቅልጥፍና በመለሳት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ረገድ በአንፃራዊነት የተሻለ ፉክክር የታየበት ነበር፤ በሙከራ ረገድ የጦና ንቦቹ ሙሉ ብልጫ ወስደዋል። በተለይም ግብ አስቆጣሪው ቢንያም ፍቅሩ ያመከናቸው ያለቀላቸው ዕድሎች የቡድኑን መሪነት ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ነበሩ። አጥቂው ዘላለል አባተ አመቻችቶለት ወደ ግብነት ያልቀየራት ኳስ ጨምሮ ሁለት ድንቅ ሙከራዎች አድርጓል።

በተጨማሪም ባዬ ገዛኸኝና አበባየሁ ሀጂሶ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ይጠቀሳሉ። በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ሀምበሪቾዎች በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ይህ ነው የሚባል ጥራት ያለው የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀምበርቾው አሰልጣኝ መላኩ ከበደ በመጀመሪያው አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ተጽዕኖ ሥር እንደነበሩ ከዕረፍት መልስም ያደረጉት የተጫዋቾች ለውጥ እንደሚፈልጉት እንዳልነበር ሲጠቁሙ የሚጠበቅባቸውን እንዳላደረጉም ተናግረዋል።

የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በበኩላቸው በጨዋታው በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ብልጫ እንደነበራቸው እና ያሰቡትንም እንዳሳኩ ነገር ግን አሁንም በተለይም በቢኒያም ፍቅሩ ላይ የአጨራረስ ችግር እንዳለ ሲናገሩ ለወጣቱ አጥቂም አድናቆታቸውን እና ወደፊት የተሻለ ተጫዋች እንደሚሆን ገልጸዋል።