“ይህ ዕድል በመሳካቱ በጣም ነው ደስ ያለኝ ፣ ደጋፊውን በጣም ነው የማመሰግነው” አቤል ያለው

የግብፅ ፕሪምየር ሊግን እየመራ ያለውን ዜድ ክለብን በሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ውል የተቀላቀለው አጥቂው አቤል ያለው ስለተሰማው ስሜት ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳቡን ሰጥቷል።

እግርኳስን ከአቃቂ ነው የጀመረው ፤ በመቀጠል በሐረር ሲቲ በአንደኛ ሊጉ የመጫወት ዕድልን ካገኘ በኋላ ራሱን በይበልጥ እያዳበረ በመምጣቱ ከሁለት ዓመት የሐረር ቆይታ መልስ በሁለት ዓመት ኮንትራት ደደቢትን ተቀላቅሎ በክለቡም አሳልፏል። በደደቢት የመጀመሪያ ዓመት ቆይታው በውሰት ውል ወደ ጎንደሩ ክለብ አምርቶ የፋሲል ከነማን መለያ በመልበስም የአንድ ዓመት ቆይታን አድርጎ በድጋሚ በደደቢት የእግር ኳስ ህይወቱን ቀጠለ በ2010 ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶት ሀገሩን ማገልገል የቻለው ፈጣኑ የመስመር እና የፊት መስመር አጥቂው አቤል ያለው ከ2011 ጀምሮ ለስድስት ዓመታት ያህል በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ከክለቡ ጋር ያሳለፈ ሲሆን 2014 እና በ2015 የውድድር ዘመን ከክለቡ ጋር የሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎም ስሟል። በዘንድሮው የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እያሳለፈ የነበረው እና በአሁኑ ሰዓትም ሊጉን በ8 ግቦች እየመራ የነበረው አጥቂው ስድስት ቀሪ ወራት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እያለሁ የግብፅ ሊግን እየመራ በሚገኘው ዜድ ክለብ በመፈለጉ በትላንትናው ዕለት ሌሊት በሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ውል በይፋ ክለቡን ተቀላቅሏል። ተጫዋቹም አጠር ባለ መልኩ ለሶከር አትዮጵያ የተሰማውን ስሜት ይናገራል።

“ይህ ዕድል በመሳካቱ በጣም ነው ደስ ያለኝ ፣ ደጋፊውን በጣም ነው የማመሰግነው ፣ በጥሩም በመጥፎም ጊዜ ከክለቡ ጋር ነበርኩኝ በብዙ ነገሮቼ ክለቡን አገልግያለሁ ብዬ አስባለሁ። ከዚህ በኋላ ከክለቡ ጋር አብሬ ባልሆንም ጥሩ ነገሮች እንዲገጥሙት እመኛለሁ። ከዚህ በፊትም እንደዚህ ዓይነት የውጪ ዕድሎች ይመጡልኝ ነበር ግን ሳላስበው ይበላሹብኛል። አሁን የተሻለ ጊዜ መጥቶ ከሀገር ወጥቼ ልጫወት ነው በሀገራችን እግር ኳስ ከጥቂት ተጫዋቾች በስተቀር ይሄን ዕድል ያገኘ የለም። ይህ ዕድል በእኔ ደርሶ በማሳካቴ ፈጣሪን አመሰግናለሁ ከዚህ በኋላ በርቶቼ የተሻለ ነገር ለመስራት አስባለሁ። በጊዮርጊስ ቆይታዬ አስቸጋሪ ጊዜን አሳልፈናል ፣ ዋንጫ እስከምንበላ ድረስ ፤ ያ ዋንጫ የበላንበት ዓመት ለእኔ ትልቁ ስኬቴ እርሱ ነበር። ዘንድሮ ኮከብ ጎል አግቢ ነኝ በዚሁ ለመጨረስ ጉጉቱም ነበረኝ ሆነም ቀረም መጨረሻው ውጪ ወጥቶ መጫወት ሆነ ይህንን ፈጣሪ ስላመጣው በጣም ደስተኛ ነኝ።”