አዲሱ ኮከብ ስለ እግር ኳስ ህይወቱ ይናገራል

የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አንተነህ ተፈራ በእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ዘለግ ያለ ቆይታ አድርጓል።

የእግርኳስ ህይወት ህልሙን መኖር የጀመረው በ2014 መጨረሻ ሐምሌ ወር ላይ ሀዋሳ በተካሄደ የኢትዮጵያ ክልል ሻምፒዮና ውድድር ላይ ነበር። አንተነህ በውድድሩ ላይ ከጨዋታ ጨዋታ የሚያሳየው መሻሻል እና ጎል የማስቆጠር አቅሙ እየጨመረ ሄዶ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች እና ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቅ ችሏል። በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ በሚካሄደው በዚህ የክልል ሻምፒዮን ውድድር ላይ በየጨዋታው የማይቀሩት የወቅቱ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ዕይታ ውስጥ በመግባት ለአስራ አምስት ቀናት የተሰጠውን የሙከራ ጊዜ በተገቢው ሁኔታ በማጠናቀቁ ለሦስት ዓመት ውል በ2015 መጀመርያ ኢትዮጵያ ቡናን መቀላቀል ችሏል። ባሳለፍነው ዓመት ካገኘው የመጫወት ዕድል ዘንድሮ የተሻለ የመጫወቻ ጊዜ ያገኘው አንተነህ ከአስራ አንደኛው እና ከአስራ ሁለተኛው ሳምንት ጀመሮ ተከታታይ ጎሎችን ለኢትዮጵያ ቡና በማስቆጠር ቡድኑን ውጤታማ ማድረግ ከመቻሉም ባሻገር ክለቡ ባሸነፈበት የመጨረሻ ጨዋታው በሊጉ የመጀመርያውን ሀት-ትሪክ ያገኘበት ሦስት ማሸነፍያ ጎሎችን ማስቆጠር ችሎ ነበር።

የብዙዎች የትኩረት ማዕከል እየሆነ የመጣው እና ከፍተኛ ዕደገት እያሳየ የሚገኘው አንተነህ ትናት ስላለፈበት የእግርኳስ ህይወቱ ዛሬ ስለሚገኝበት አቋም እና ወደፊት ስለሚያስበው ዕቅዱ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል እኛም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

በሶከር ኢትዮጵያ የመጀመርያህ ቃለ መጠይቅህ ነውና ጥያቄዬን ትውልድህ የት ነው ? ለቤተሰቦችህስ ስንተኛ ልጅ ነህ ? ከሚል ልጀምር ?

“እሺ አመሰግናለው። ትውልዴ እና ዕድገቴ አዱላ ኦዬ በተባለች ከተማ ነው። ለቤተሰቤ የመጀመርያ ልጅ ነኝ ከእኔ በታች ሦስት ታናናሽ እህት እና ወንድሞች አሉኝ። እግርኳስን ተጫውቶ ያለፈ ከቤተሰቦቼ መሐል ባይኖርም እናቴ እና አባቴ በጣም ስፖርትን የሚወዱ ናቸው። በተለይ አባቴ ለእግርኳስ ልዩ ፍቅር ያለው ሰው ነው።”

ከቤተሰቦችህ እግርኳስን ተጫውቶ ያለፈ ከሌለ እንዴት ወደ እግርኳስ ተጫዋችነቱ ልታዘነብል ቻልክ ?

“ቅድም እንዳልኩሁ ቤተሰቦቼ ስፖርትን የሚወዱ ፣ ለስፖርት የቀረቡ ሰዎች መሆናቸው ወደ እግርኳሱ እንዳዘነብል የረዳኝ ይመስለኛል። ቤተሰቦቼ በየትኛው ስፖርት ውስጥ ተሳትፎ አድርገው ያላለፉም ቢሆንም እግርኳስን እየተጫወትኩ ትምህርቴን ደግሞ ጎን ለጎን ዕኩል አድርጌ እንድጓዝ በጣም ነው ይደግፉኝ ፣ ያግዙኝ የነበረው። በተለይ አባቴ ሰፈራችን አካባቢ ኳስ መጫወቻ ሜዳ በመኖሩ ከልጅነቴ ጀምሮ ይዞኝ እየሄደ እንድጫወት ያበረታታኝ ነበር። በዲኤስ ቲቪ የተለያዩ ጨዋታዎችንም አብረን ቁጭ ብለን እናይ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ አባቴ ሜዳ ነው የሚውለው ማለት ይቻላል። እግርኳስን በጣም ነው የሚወደው።”

አባትህ ወደ ሜዳ ይዞህ ይሄዳል በዲኤስ ቲቪ ጨዋታዎችን ከመከታተል በተጨማሪ በተወለድክበት አካባቢ ከፍ ያሉ የሰፈር ውድድሮች ነበሩ። ሌላ አንተን ወደ እግርኳስ ተጫዋችነት የሚገፋፉ ተጫዋቾች ነበሩ ?

“ብዙ ውድድሮች የሉም ነገር ግን የሚገርምህ እኔ ራሴን ሁሌም ኳስ ውስጥ እንዳለው ነው የማቀው እንጂ መቼ እግርኳስ እንደጀመርኩ አላውቅም። የከተማችን ቡድን አለ። እንዲሁም በዛን ሰዓት ብዙ ዕድሎች ባይፈጠሩም ፕሮጀክት ውስጥ ገብተው ሲጫወቱ የማቃቸው አሉ እነርሱ የሚያደርጉትን አይ ነበር። ከዚህ ውጭ የከተማችን ቡድን ብሔራዊ ሊግ ሲጫወት አንድ ዘመድ አለን ዝምድናው ምን እንደሆነ ግን አላቅም እርሱ ሲጫወት ደስ ይለኝ ነበር። የመስመር አጥቂ ነው በጣም ጎበዝ ነው ጎል ያገባ ነበር። እናም በእርሱ አጨዋወት እና ጎል የሚያገባበት መንገድን እያየሁኝ የተሳብኩኝ ይመስለኛል። እንዲሁም ፈቱዲን ጀማል፣ ዳዋ ሆቴሳ ሲጫወቱ አይ ነበር። ኳስም እኔ አመላልስ ነበር። እና ለቤታችን ኳስ መጫወቻው ቅርብ በመሆኑ እኔን ወደ እግርኳሱ እንድገባ ረድቶኛል ብዬ አስባለው።”

የእግርኳስ ሀ ሁ ወይም ፕሮጀክት ታቅፈህ የእግርኳስን መሰረታዊ ሥልጠናዎችን መቼ መውሰድ ጀመርክ ?

“ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድን 2011 እና 2012 ነው። ይህ ማለት ስልጠና ውስጥ ገብቼ መሰልጠን ሳይሆን ከተወለድኩበት አካባቢን በመወከል ለኦሮምያ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ውድድር መጫወት ጀመርኩኝ። ይህ ማለት ትምህርት እንማር እና ትምህርት ሲዘጋ ክረምት ላይ በአንድ በተመረጠ ከተማ ውድድሩ ይካሄዳል ፤ በአካባቢያችንን ተመርጠን ለዚህ ውድድር እንሄዳለን። ሁለቱን ዓመታት በዚህ መልኩ ነው ያሳለፍኩት። ከዛ በኋላ ነው በ2013 ለተወለድኩበት ከተማዬ ለአዶላ ወዩ ቡድን በቢጫ ቲሴራ ለመጫወት ቻልኩ።”

ከ2011 በፊት የልጅነት ህይወትህን በፕሮጀክት ታቅፈህ የወደሰድከው ስልጠና የለም ማለት ነው ?

“እንደዛ የለም። ቅድም እንዳልኩህ ሰፈር ሲጫወቱ እያየሁ ኳስ እያመላለስኩኝ እኔም በግሌ እንደነርሱ ለመሆን ስጥር ከፍ እያልኩ ስሄድ ራሴ ከማደርገው እንቅስቃሴ ውጭ የስልጠና መርሐ ግብር ወጥቶ በሳምንት ሁለቴም አልያም ሦስት ቀን ስልጠናዎችን እየሰለጠንኩኝ አላደኩኝም። ያው የምኖርበት አካባቢ ብዙም እንደዚህ ያሉ ነገሮች የተሟሉበት አይደለም። ሁሉ ነገር በራሳችን ጥረት ነው ስንጫወት ያደግነው።”

ታዲያ ማነው የወደፊት አቅምህን አይቶ ለኦሮምያ ከ17 ዓመት በታች ውድድር እንድትመረጥ ያደረገህ ?

“በዚህ ረገድ አንድ አሰልጣኝ አለ ፤ ወርቁ ገመዳ ይባላል። አሁንን የአቤሎ ወዩ ከተማ አሰልጣኝ ነው። እርሱ ነው ከ17 ዓመት በታች ቡድን መርጦኝ የወሰደኝ በኋላም ለአቤሎ ወዩ ቡድን አሳድጎኝ ለኦሮምያ ከፍተኛ ዲቪዚዮን ቡድን እንድጫወት ያደረገኝ።”

ልጅነትህ ጀምሮ ትጫወትበት የነበረው ቦታ ላይ ነው አሁንም በኢትዮጵያ ቡና እየተጫወት ያለህው ?

“አዎ እኔ በሁለት እግሮቼ መጫወት ይቀለኝ ስለነበረ አሁን የምጫወትበት ቦታ ነው ልጅም ሆኜ እጫወት የነበረው። በተለይ ከግራ የማጥቂያ መስመር አመዝኜ አጥቂ ሆኜ በብዛት እየተጫወትኩኝ ነው ያደኩት። በዚህ መንገድ ስጫወት በጣም ጎል አገባ ነበር። በተጨማሪም የፊት አጥቂ እንዲሁም የአጥቂ አማካይ በመሆን እጫወት ነበር። በአጠቃላይ ነፃ ሚና ተሰጥቶኝ እየተጫወትኩ ነው ያደኩት። እኔ በባህሪዬ ቆሞ መጫወት አልወድም። በተለያዩ የማጥቃት መስመሮች ሁሉ እንቀሳቀስ ነበር። በተለይ ተቃራኒ ቡድን ኳስ እንዳይጀምሩ በፍጥነት እየተራሯጥኩ በተለያዩ ቦታዎች ፕሬስ አድርግ ነበር። በዚህ አጋጣሚ እንደያውም ከእኔ ጋር ከሚጫወቱ ልጆች ጋር በተደጋጋሚ የቦታ ሽግሽግ አደርግ ነበር። ስለዚህ ያንን ባላንስ ለማደርግ ነፃ ሚና ተሰጥቶኝ እጫወት ነበር። አሁንም ኢትዮጵያ ቡና ከመጣው ጀምሮ የምጫወትበት ቦታ ከልጅነቴ ጀምሮ እጫወትበት የነበረው ቦታ ነው እየተጫወትኩኝ ያለሁት።”

ወደ ኢትዮጵያ ቡና የመጣህበት መንገድ እንዴት ነው ?

“ቅድም እንዳልኩህ ከተወለድኩበት ከተማ ከአዶላ ወዩ በኦሮሚያ ሊግ ውድድር ሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ለኦሮሚያ ከፍተኛ ዲቪዚዮን ሻኪሶ ከተማን በመወከል ጅማ ከተማ ላይ የሚደረገውን የማጣርያ ውድድርን ሦስተኛ ሆነን ስናጠናቅቅ እኔም በግሌ ስምንት ጎሎችን በማስቆጠር የውድድርሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ሽልማት ተሸልሜ ለኢትዮጵያ ክልል ሻምፒዮን ውድድር ለሻኪሶ ከተማ ለመጫወት በ2014 መጨረሻ ላይ ሀዋሳ ውድድር ላይ መጣሁኝ። በዛም ውድድር በሰባት ጎል በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አግቢ እና ኮከብ ተጫወች ሆኜ አጠናከኩኝ። ከዚህ ውድድር ነው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ለኢትዮጵያ ቡና የመረጠኝ። በወቅቱ እኔ ብቻ አልነበርኩም ፤ ሌላም ልጅ ነበር። የሙከራ ጊዜ ተሰጠን እኔ ቀረሁኝ በዚህ መልክ ነው በ2014 መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀልኩት።”

ያኔ ልጅ ሆነህ አልያም በኦሮሚያ ሊግ ስትጫወት እዚህ ደረጃ እደርሳለው ብለህ ታስብ ነበር ?

“አዎ በጣም አስብ ነበር። ከእኛ አካባቢ ወጥተው ትላልልቅ ክለቦች ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብዙም ባይኖሩም ፣ ፕሮጀክቶች አለመኖራቸው እንዲሁም አሰልጣኞች በብዛት ባይኖሩም ግን የሆነ ቀን ትልቅ ተጫዋች እንደምሆን አስብ ነበር። በጣም ጠንክሬ እሰራ ነበር። አባቴም ወደ ተለያዩ ክለቦች ወጣ ብዬ እንድጫወት ዕድሎች እንዲመቻችልኝ ይጥር ነበር። ግን ያም ቢሆን ሰብሮ ለመውጣት በጣም ከባድ ነበር። ከዛ ግን ከእኛ ሀገር ፈቱዲን ጀማል ወጥቶ በትልቅ ክለብ ደረጃ መጫወት ጀመረ። እንደ አጋጣሚ እርሱ በ2012 ኢትዮጵያ ቡና ዋና ቡድን እየተጫወተ ስለነበር ጠርቶኝ አዲስ አበባ በመሄድ ከ17 ዓመት በታች ኢትዮጵያ ቡና ቡድን ለሙከራ አንድ ሳምንት ቆየሁኝ እንዳጋጣሚ ሆኖ ሳይሳካልኝ ለመቀነስ ቻልኩኝ።”

ከዓመታት በፊት ለሙከራ መምጣትህን ተከትሎ አንተ እና ኢትዮጵያ ቡና ትስስር ቆየ ከጀመረ ማለት ነው ?

“አዎ በወቅቱ ሙከራውን ፈቱዲን አመቻችቶልኝ መጣሁኝ እንደ አጋጣሚ ሙከራው ወደ ማለቂያው አካባቢ ስለነበር በሰባት ቀን ውስጥ ነው ያዮኝ። ያው ሳይሳካ ብመመለስም የሚገርም ነገር አንድ ቀን መጥቼ የኢትዮጵያ ቡና መለያን እንደምለብስ ለራሴ እነግረው ነበር። ምክንያቱም ከልጅነቴ ጀምሮ ቡናን እየደገፍኩ ነው ያደኩት። ክለቡን ደጋፊዎቹን በጣም ነው የምወደው እና ከ17 ዓመት በታች ቡድን ተቀንሼ ብሄድም ውስጤ ግን አንድ ቀን ይሳካልኝ እንደሚችል ይነግረኝ ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ ዳግም በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና እኔን ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሲጠራኝ ሌሎች የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች እንዲሁም የከፍተኛ ሊግ ቡድኖች ሀዋሳ ላይ የተመለከቱኝ እኔን ለመውሰድ ብዙ ጥያቄዎች ዕድሎች ነበሩ ግን ምርጫዬ ያደረኩት ኢትዮጵያ ቡና ነበር። ቡና ሲባል የሆነ የሚሰጥህ ስሜት አለ ከልጅነቴ ጀምሮ እደግፈው ስለነበረ ቡና ሲባል ካሉት ነገሮች ሁሉ ለእርሱ ቅድሚያ ትሰጣለህ። ምክንያቱም የሀገሪቷ ተወዳጅ ክለብ ስለሆነ ወደ ቡና አመራሁኝ እንደ አጋጣሚም ቡና ዝግጅቱ ሀዋሳ ከተማ ስለነበረ አስራ አምስት ቀን የሙከራ ጊዜ ካሳለፍኩ በኋላ ፊርማዬን ለኢትዮጵያ ቡና ማኖር ችያለው።”

ከዚህ ቀደም ከ17 ዓመት በታች ቡድን መጥተህ ሙከራ አድርገህ ተቀንሰህ ነበር በድጋሚ ከሦስት ዓመት በኋላ ዋናው ቡድን ሙከራ ስታደርግ እቀነሳለው ብለህ አልሰጋህም ነበር ?

“በፍፁም አላሰብኩም ፤ ዕድሉን በራሱ ማግኘቴ ለኔ ትልቅ ስኬት ነው። ምን አልሰጋሁም ፕሪሚየር ሊግ ክለብ ጠርቶኝ የሙከራ ጊዜ ሲሰጠኝ የበለጠ ተነሳሽነት እና በራስ መተማመኔን ነው የጨመረው አዕምሮዬ ውስጥ እንዲህ ያለ ስጋት አልመጣብኝም። ምክንያቱም እኔ በእግርኳስ ህይወቴ አንደኛ ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ አልተጫወትኩም። በቀጥታ ነው ፕሪሚየር ሊግ የተቀላቀልኩት ስለዚህ ይህን ያገኘሁትን ትልቅ ዕድል ለመጠቀም ማድረግ ያለብኝን ዝግጅቶች ሁሉ ሳደርግ ነው የቆየሁት ከጎኔም በጣም የሚመክሩኝ የሚደግፉኝ ሰዎች ነበሩ። በተለይ ፈቱዲን ጀማል እና አሰልጣኝ አንዱዓለም በጣም ያበረታቱኝ ስለነበር እንደሚሳካ አስብ ነበር።”

በቀጥታ ሁለት የሊጉን የውድድር እርከኖችን በማለፍ ሙከራህን በስኬት አጠናቀህ በቀጥታ የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ስትሆን ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብህ ?

“ይህን መግለፅ አይቻለም። በጣም ልዩ ነበር። ማለት እኔጃ ብቻ እኔ ብቻ ሳልሆን የተወለድኩበት ሀገሬ ሰዎችም ጭምር ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸው ነበር። ምክንያቱም ኦላይን የምጠቀማቸው ነገሮች ነበሩ ፤ ብዙ ሰዎች ከጎኔ እንደነበሩ ያበረታቱኝ ስለነበር ደስታው ልዩ ነበር። በተለይ ደግሞ ለእኔ ብዙ ዋጋ የከፈሉ ቤተሰቦቼ አባቴ እና እናቴ የተደሰቱን ደስታ ሳይ ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። አዲስ አበባ ሄጄ ፈርሜ ወደ ሀዋሳ ለዝግጅት ስመለስ ሰዎች እየደወሉ ቤተሰቦቼ ጋር ‘እንኳን ደስ አላችሁ’ እያሉ ሲያወሯቸው ይህ ደስታው ከምንም በላይ ነው። ትልቁ የኔ ደስታ የቤተሰቦቼን ደስታ ማየት ነበር።”

በኢትዮጵያ ቡና የመጀመርያ ጨዋታህን እና ጎልን ወደ ኋላ ሄደህ አስታውሰኝ ?

“የሲቲ ካፕ ውድድሩን ሳይጨምር በፕሪሚየር ሊጉ ዓምና ባህር ዳር ከተማ ላይ እ ከወልቂጤ ከተማ ጋር በነበረ ጨዋታ ነው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ተቀይሬ እንደገባ ያደረገኝ ፤ ይህ ዕለት ለእኔ ልዩ ትዝታ አለው ፤ የሊጉ የመጀመርያ ጨዋታዬ ስለነበር። አሰልጣኝ ተመስገንም በተደጋጋሚም ይመክረኝ ነበር። ምክንያቱም በእኔ ቦታ ብዙ ተጫዋቾች ፈርመው ስለመጡ ዕድሎችን እስካገኝ ድረስ በርትቼ እንድሰራ ይመክረኝ ነበር። ሁለተኛ ጨዋታዬን ከአርባምንጭ ጋር ተጫወትኩኝ እንደአጋጣሚ መስፍን ታፈሰ በጉዳት አስራ ሰባተኛው ደቂቃ ሲወጣ ተክቼ ተቀይሬ ገባሁ። በዚህም የሊጉን የመጀመርያ ጎሌን አስቆጥሬያለሁ። ይህንንም ቀን እኔ አረሳው ምክንያቱም በተለየ ሁኔታ ጎል በማስቆጠር ራሴን ያስተዋወኩበት ስለሆነ ትዝታው ከባድ ነው። በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን ማመስገን እፈልጋለሁ። እርሱ ነው ዕድሎችን በማመቻቸት አሁን ለደረስኩበት ደረጃ መነሻ የሆነኝ።”

ከክልል ሻምፒዮን ነው በቀጥታ ወደ ሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን የመጣኸው ይህ የመሆኑ ያጋጠመህ ተግዳሮት አለ ?

“ያው እንደመጣው ብዙ የመጫወት ዕድሎችን በተደጋጋሚ የማላገኝ ስለነበረ ይህ ትንሽ አለመጫወቴ አዲስ ሆኖብኝ ነበር። በአንዴ የመጫወት ዕድል ማግኘት አለብኝ ከሚልም አልነበረም። አውቃለው በአንዴ ነገሮች ሊመቻቹ እንደማይችሉ ሆኖም ለመጫወት ካለኝ ጉጉት እና ጠንክሬ በመስራት ዕድሎችን በማግኘት ራሴን ለማስተዋወቅ በጣም እፈልግ ስለነበረ ትንሽ እጨናነቅ ነበር። ያው ከጎኔ ብዙ ሰዎች ስለነበሩ ይመክሩኝ የመጫወት ዕድል እስካገኝ ድረስ ምን ማደረግ እንዳለብኝ ያሳዩኝ ነበር። ያው እንደምታቀው እዚህ ሊግ ላይ ሁሉ ነገር በምክንያት ነው የሚሰራው ታክቲካል ስራዎች አሉ። እኔ በዚህ መንገድ አላለፍኩም የተቃራኒ ቡድንን እንቅስቃሴ ማየት፣ የራስን ቡድን ጨዋታ ቪዲዮ መመልከት ብቻ የማያቸው ነገሮች ልምምድም ጨምሮ ብዙ የተለዩ ነገሮች አሉ እና አዲስ ሆኖብኝ ነበር። ያው በቀለም ትምህርቴ ጥሩ የነበርኩ ስለሆነ ይመስለኛል ነገሮችን በፍጥነት ለመረዳት አልከበደኝም። በአጠቃላይ አሰልጣኞቼ አባቴ ሌሎች ከጎኔ የነበሩ ሰዎች ትዕግስት አድርግ በማለት ይመክሩኝ ስለነበር እሺ እላቸዋለው። በፀባዬም አስቸጋሪ ስላልሆንኩ ወደ ፊት ዕድሎች እንደሚመጡ ተስፋ አደርግ ስለነበረ በወቅቱ የነበሩ ፈተናዎችን አልፌያቸዋለው። አሁንም ቢሆን የማገኛቸውን ዕድሎች ለመጠቀም እየሞከርኩ ነው።”

የቀለም ትምህርት ላይ ውጤታማ እንደሆንክ በቅድሙ ጥያቄ ላይ ጠቆም አድርገህልኝ አልፈህ ነበር። እስከ ምን ድረስ በትምህርትህ መዝለቅ ችለህ ነበር ?

“እንደ አጋጣሚ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ ቡና በተጠራሁኝ ጊዜ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት መጥቶልኝ ነበር። ያው እግርኳስን በጣም እወድ ስለነበርና መድረስ የምፈልገው ቦታ ስለነበረ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባት ይልቅ ቡናን መርጬ ትምህርቱን ለማቆም ወሰንኩ።”

በቀጣይ በርቀትም ይሁን በሌላ ፕሮግራሞች ትምህርትህን የመቀጠል ሀሳብ አለህ ?

“ነገሌ አርሲ ዩኒቨርስቲ ነበር የተመደብኩት። በቀጣይ ነገሮች ሲስተካከሉልኝ ትምህርቴን የመቀጠል ሀሳብ አለኝ። አሁን ትኩረቴ ያለሁበት የእግርኳስ ህይወትን መስመር ማስያዝ ነው። ነገሮች መስመር ሲይዙልኝ ማለትም በእግርኳስ የሆነ ነገር ማስቀመጥ አለብኝ። ይህ ማለት ወደ ኢትዮጵያ ቡና ስመጣ የፊርማ ያገኘሁት ጥቅም የለም። ዋና ዓላማዬ ራሴን ማሳየት ላይ ነው ትኩረት ያደረኩት ገና ራሴንም ለማሳየት ብዙ ሥራ ይቀረኛል፤ ያንን ማድረግ እፈልጋለሁ። እኔን ደክመው ያሳደጉኝን ቤተሰቤን መርዳት እፈልጋለው። ስለዚህ በትምህርቴን ለመቀጠል የማስባቸው ነገሮች አሉ። ግን ሁሉን ነገር በአንዴ ማድረግ ከባድ ነው። አሁን ሀሳቤን ወደ ኳሱ አድርጌ በቀጣይ ትምህርቴን ለመማር አስባለሁ።”

በሊጉ ሁለተኛ ዓመትህ ላይ ትገኛለህ። አንተነህ ከዓምናው ዘንድሮ ምንድነው ልዩነቱ ?

“ከዓምናው ዘንድሮ ብዙ የተለየ ነገር ኖሮ ሳይሆን አሁን በተለይ በዚህ ዓመት መጀመርያ አካባቢ ካለው ነገር አንፃር ከታክቲክ አኳያ ከአሰልጣኙ የጨዋታ መንገድ አንፃር ዓምናው ዘንድሮ ብዙ ከጨዋታ ርቄ ነበር። ያው በትዕግስት እየሰራው እጠብቅ ነበር። ልጆች እየተጎዱ ሲመጡ አልፎ አልፎ የመጫወት ዕድል አገኝ ነበር። ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ አሰልጣኝ ነፃነት ያውቀኝ ስለነበር ተደጋጋሚ ዕድሎችን እየሰጠኝ መጥቻለሁ። የመጫወት ነፃነት ሲሰጠኝ፣ በራስ መተማመኔ እየጨመረ አብረውኝ ከሚጫወቱ ልጆች ጋር ሜዳ ላይ እየተግባባን ስንመጣ እኔም በተደጋጋሚ እንደነገርኩህ የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም የምችለውን ለማድረግ በከፍተኛ ትኩረት ነው ወደ ሜዳ የምገባው። በአጠቃላይ ከአምናው በንፅፅር የዘንድሮው የተሻለ እያደረግኩ እገኛለሁ።

የመጫወት ነፃነት ሰጥቶኛል ስትል የአሰልጣኝ ለውጡ ጠቅሞኛል እያልክ ነው ?

“እንደዛ ለማለት ሳይሆን አሁን ባለው ነገር ተደጋጋሚ ብዙ የመጫወት ዕድሎችን እያገኘው መሆኑ እንጂ የአሰልጣኝ ለውጥ አይደለም። እኔም የተሰጠኝ ዕድሎችን በቀላሉ ላለማጣት ጠንክሬ በመስራቴ ያገኘሁት ነው ብዬ የማስበው። ዓምና ዓመቱን ሙሉ በመጀመርያ አስራ አንድ ውስጥ ተካትቼ የተጫወትኩት ስድስት አይሞላም። ወደ ስምንት መቶ ደቂቃ ያህል ተጫውቻለሁ። ዘንድሮ ወደ አራት ጨዋታ በቋሚነት ተጫውቻለው፤ ከዓምናው ዘንድሮ ብዙ የመጫወት ሰዓት አገኛለው ብዬ አስባለው። ዓምና በውድድር ዓመቱ አራት ጎል አስቆጥሬ ነው ያጠናቀኩት። ዘንድሮ እስከ አሁን አስራ ሦስተኛው ሳምንት ድረስ አምስት ጎሎች አስቆጥሬያለሁ።”

ትክክለኛ የመጫወቻ ቦታዬን አግኝቻለሁ ብለህ ታስባለህ ?

“አሰልጣኞቼ በሰጡኝ ቦታ ለመጫወት ዝግጁ ነኝ ፤ እኔ ከፊት መስመር በሁሉም ቦታዎች ላይ ለመጫወት ዝግጁ ነኝ። ዋነኛው ዓላማዬ በሜዳ ላይ የማገኛቸውን ዕድሎች ለመጠቀም ዝግጁ መሆን ነው።”

ጎል ማስቆጠርህን እስከ ምን ድረስ ማድረስ ትፈልጋለህ ?

“ፈጣሪ ረድቶኝ በእኔ ጎሎች ክለቤ እያሸነፈ ነው። ከዚህ በኋላም ዕድሎች የሚሰጡኝ ከሆነ ክለቤን መጥቀም እና ከዚህ በላይ ራሴን ማሻሻል እፈልጋለው። ጎል አካባቢ ጨራሽ ለመሆን እሰራለሁ። አሁን የሚሰማኝ ነገር ገና ብዙ የሚቀረኝ ነገር እንዳለ ነው። ዕድሎችን ካገኘው ራሴን በቋሚ ቦታ ለማስቀመጥ ከፈጣሪ ጋር አሁን ካለኝ ነገር የተሻለ ነገር መስራት እፈልጋለው። ይሆናልም ብዬ አስባለው።”

የመጀመርያህን ሀት ትሪክ ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ መድን ላይ መሥራት ችለሀል። ይህ ምን አይነት ስሜት ነበረው ? ለቀጣይ የእግርኳስ ህይወትህ ምን ይነግርሀል ?

“አዎ የመጀመርያ ሀት ትሪክን ሰርቻለው። በጣም ደስ ብሎኛል። ይበልጥ ደግሞ የእኛ ደጋፊዎች ሲደሰቱ ማየት በራሱ የሚሰጠው ነገር አለ። ክለባችን ጫና ውስጥ ነበርን፤ ከዛ ጫና ለመውጣት ብዙ ስንሰራ ቆይተናል። ይህ በተወሰነ መልኩ ተሳክቶልናል። ብዙ የሚቀረን ነገር አለ፤ እርሱን እያስተካከልን እንሄዳለን። በአጠቃላይ እኔ ሀት ትሪክ ሰርቼ በማሸነፋችን በጣም ደስ ብሎኛል። ብዙ ተስፋ ነው በውስጤ የጨመረው። ከኔ ጀርባ ብዙ የሚደግፉኝ የሚረዱኝ ሰዎች ስላሉ እነርሱ እንዲደሰቱ ማድረጌ የበለጠ ደስታዬን ጨምሮታል።”

አሁን የሁሉም የትኩረት ማዕከል አንተ ሆነሀል። አሁን ያለህበት አቋም ጥሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እውቅናዎች የምታይበት ሁኔታ እንዴት ነው ?

“ይህ ያው እንደ አንተ አያያዝ የሚወሰን ነው ፤ ብዙ ጊዜ ሰዎች በሙገሳዎች ሲጠፉ ተመልክተናል። በተቃራኒው ደግሞ በዚህ ሳይገቱ ትልቅ ቦታም የደረሱ አለ። አሁንም እኔ በዙሪያዬ ተመስገን ዳናን ጨምሮ ብዙ ሰዎች አሉ፤ አሁን ድረስ እየደወለ ያወራኛል። እኔም በግሌ ገና ምንም እንዳልጀመርኩ ነው የሚሰማኝ። በግሌ ፈጣሪ ከፈቀደ የተሻለ ነገር የመስራት ዕቅድ አለኝ ፤ ዘንድሮ ከአምናው በተሻለ ነገሮችን ለማድረግ እየሞከርኩ ነው በቀጣይም ከዚህ በላይ ራሴን አሳድጌ ብሔራዊ ቡድኑንም ማገልገል እፈልጋለሁ።”

ስለ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ምን ታስባለህ ?

“ማንኛውም በሊጉ የሚጫወት ተጫዋች ጥሩ ብቃቱን አሳይቶ ብሔራዊ ቡድኑን ማገልገል የማይፈልግ የለም ፤ እኔም አንዱ ዓላማዬ ራሴን በብሔራዊ ቡድን ማሊያ ማየት እና ለሀገሬ ይህን አድርጊያለሁ የሚለውን ታሪክ መፍጠር እፈልጋለሁ። ከፈጣሪ ጋር ያለኝን ነገር አሳድጌ ሀገሬን በየትኛውም እርከን ማገልገል ነው። መች እንደሆን ባላውቅም አንድ ቀን ብሔራዊ ቡድኑን እንደማገለግል አውቃለሁ።”

አቅምህን ለማሳደግ በግልህ ምን ያህል ትሰራለህ?

“በቡድን ከምንሰራው ልምምድ ባለፈ በሚኖሩኝ ጊዜዎች በግሌ ከአጨራረስ ጋር የተያያዙ ስራዎችን እሰራለሁ። በቀጣይም አሁን ላይ በዚህ ረገድ ማሻሻል አለብህ። ብለህ ሰዎች በሚሰጡኝ አስተያየቶች ላይ አቅም በፈቀደ መልኩ ስራዎችን በመስራት የተሟላ አጥቂ ለመሆን አልማለሁ።”

እዚህ ለመድረስህ የቤተሰቦችህ እገዛ ምን ያህል ነው?

“ስለቤተሰቦቼ እንዲህ ነው ብዬ የምጨርሰው ነገር የለም ፤ በትምህርቴም ሆነ በእግር ኳሱ እንድገፋ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። የቤቱ ቀዳሚ ልጅ ነኝ። እኔም ሆነ ሌሎች አራት ታናናሾቼ የምፈለገውን ነገር አጓድለውብን አያውቁም። አባቴ አንድም ቀን የሚያስፈልገኝን ነገር ነግሬው አላውቅም። ሁሌም ቢሆን ሳልጠይቀው ነው የሚያደርግልኝ። በአጠቃላይ ብቻ ውለታቸው ፈጣሪ ይክፈላቸው ነው ማለት የምችለው። በእኔ ደስተኛ ሆነው ከማየት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም።”

ከሀገር ውስጥ አርዓያ የምታደርገው ተጫዋች አለ?

“አዎ፤ ብዙ ተጫዋቾች አሉ። ሳልሀዲን ሰዒድ፣ ሽመልስ በቀለ እና አቡበከር ናስር የመሳሰሉ ተጫዋቾች ወደ ውጭ ወጥተው ተጫውተዋል። እኔም በጊዜ ሂደት ራሴን በሚገባ አሳድጌ እና ጠንክሬ ሰርቼ በዛ ደረጃ ስለመጫወት አስባለሁ።”

ስለ ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ምን ትላለህ?

“የኢትዮጵያ ቡናን ደጋፊ እንዲህ ነው ማለት አይቻልም። ከከተማ ከተማ እየተዘዋወሩ ቡድናቸውን የሚደግፉበት መንገድ የተለየ ነው። ለእነሱ በቡና መለያ የሆነ ነገር አድርጌ ባልፍ ደስ ይለኛል። በተቻለኝ መጠን በፍጥነት የሆነ ነገር ማድረግ ብንችል ደስ ይለኛል። እነሱ ለእኔ ሁሌም ጥሩ ናቸው እኔም ለእነሱ የሆነ ደስታን ለመፍጠር ሁሌም ቢሆን እጥራለሁ።”