መረጃዎች | 54ኛ የጨዋታ ቀን

14ኛ የጨዋታ ሳምንት ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ጅማሮውን ሲያደርግ በጨዋታዎቹ ዙርያ ተከታዮችን መረጃዎች አጠናቅረናል።

ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

9 ሰዓት ላይ ጅማሮውን የሚያደርገው ጨዋታ ከሽንፈት መልስ ወደ ድል ለመመለስ የሚጥሩትን ሲዳማ ቡናዎችን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገናኛል።

ከአስደናቂ የማንሰራራት ጉዟቸው ማግስት በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች አሁን ላይ በ15 ነጥቦች ወደ 9ኛ ደረጃ ሲንሸራተቱ የመጀመሪያውን ዙር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እና ቅዱስ ጊዮርጊስን በመግጠም የሚደመድሙ ይሆናል።

በመሆኑም ሁለት ጠንካራ ጨዋታዎች የሚጠብቃቸው ሲዳማዎች የመጀመሪያውን ዙር በዝቅታ ላለመቋጨት ወደ ቀደመ ብቃታቸው መመለስ የግድ ይላቸዋል።

ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በትዕይንቶች በተሞላው ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾቻቸውን በቀይ ካርድ ያጡት ንግድ ባንኮች የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ሽንፈታቸውን ሲያስተናግዱ በዚህም መሪነታቸውን አስረክበው በ29 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ከመጨረሻ አራት የሊግ ጨዋታቸው በሁለቱ የተሸነፉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች አሁንም ዳግም መሪነታቸውን ለመረከብ የነገውን ጨዋታ እንደ መንደርደርያ ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ባለፈው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከቱት ሱሌይማን ሀሚድ እና ፍሬው ጌታሁን በቅጣት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን በሲዳማ ቡና በኩል ደስታ ደሙ አሁንም በጉዳት የማይኖር ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 16 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን አመዛኙ 10 ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነው። ሲዳማ 4 ጨዋታ ሲያሸንፍ ንግድ ባንክ 2 አሸንፏል። ሲዳማ ቡና 18 ጎል ሲያስቆጥሩ፣ ንግድ ባንክ 19 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

የጨዋታ ሳምንቱን የመክፈቻ መርሃግብር በመሐል ዳኝነት ቢኒያም ወርአገኘሁ ሲመራው እሱባለው መብራቱ እና ሸረፈዲን አስረኪና ረዳቶች አራተኛ ዳኛ ደግሞ መለሠ ንጉሴ ሆኗል።

መቻል ከኢትዮጵያ ቡና

የምሽቱ መርሃግብር ደግሞ ሁለት ጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙትን ቡድኖች የሚያገናኝ ይሆናል።

የሰንጠረዡን አናት በ30 ነጥቦች የተቆናጠጡት መቻሎች በሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ከተሸነፉበት ጨዋታ በኃላ ባደረጓቸው አስራ አንድ ጨዋታዎች ስምንቱን ሲረቱ በተቀሩት ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ የተጋሩ ሲሆን ይህም ወጥነት ብርቅ በሆነበት ሊግ ወጥ ብቃትን እያሳዩ ከሚገኙ ቡድኖች ቀዳሚው ያደርጋቸዋል።

በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ተከታታይ ድሎችን ያሳኩት ኢትዮጵያ ቡናዎች አሁን ላይ በ22 ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን በመጨረሻ ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ያስመዘገቧቸው አውንታዊ ውጤቶች ከቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ተዳምረው በተወሰነ መልኩ ከፍተኛ ቁጭት ውስጥ ገብቶ ለነበረው ደጋፊ ተስፋን የሚፈነጥቁ ናቸው።

ከሰሞኑ አስደናቂ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አንተነህ ተፈራ በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦችን በማስቆጠር ለቡድኑ ወሳኝ ሚናን እየተወጣ ሲገኝ በነገውም ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና ማጥቃት ላይ ቁልፍ ሚናን እንደሚወጣ ሲጠበቅ የመስመር አጥቂው መስፍን ታፈሰም ምንም እንኳን ግቦችን ባያስቆጥርም በቡድኑ ማጥቃት ላይ ያለው ሚና እየጎለበተ ያለ ይመስላል።

በአንፃሩ በመቻሎች በኩል ከመስመር እየተነሳ ለቡድን የማጥቃት ጨዋታን የሚያቀጣጥለው ከነዓን ማርክነህ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ከእሱ በተጨማሪ በኃይሉ ግርማ በቅጣት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያልፈው ይሆናል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሕክምና ላይ ያለው ኃይለሚካኤል አደፍርስ ብቻ ጨዋታው የሚያመልጠው ሲሆን ጉዳት ላይ የነበሩት አማኑኤል ዮሐንስ እና ብሩክ በየነ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 32 ጨዋታዎችን አድርገው ኢትዮጵያ ቡና 16 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን መቻል 7 ጊዜ ድል አድርጎ በ9 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ቡናማዎቹ 47፣ ጦሩ 33 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ይህን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለሱስ ባዘዘው ሲመሩት ረዳት በመሆን ደግሞ ወጋየሁ አየለ እና ሙሉነህ በዳዳ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ባህሩ ተካ ተመድቧል።