ይስሐቅ ዓለማየህ ሙሉጌታ የሆላንዱን ክለብ ተቀላቀለ

ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ትውልደ ኢትዮጵያዊ ፌይኖርድ ሮተርዳምን መቀላቀሉ ታውቋል።


ከኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦች የተገኘው የአስራ ሰባት ዓመቱ አማካይ ይስሐቅ ዓለማየህ በስድስት ወራት የውሰት ቆይታ የፌይኖርድ ታዳጊ ቡድንን ተቀላቀለ። ከ Djurgården ታዳጊ ቡድን ከተገኘ በኋላ ገና በለጋ ዕድሜው ለዋናው ቡድን በመጫወት የጀመረው ይህ አማካይ ከ2022 ጀምሮ በዋናው ቡድን ደረጃ መጫወት ችሏል። ተስፈኛው አማካይ ከእናት ክለቡ ጋር እስከ 2025  የሚያቆይ ውል ቢኖረውም ከDjurgården ጋር ከመቆየት ይልቅ የሆላንዱን ታላቅ ክለብ ፌይኖርድ ከ21 ዓመት በታች ቡድን በውሰት መቀላቀልን መርጧል።

ረዥም ጊዜ እንደወሰደ የተነገረለት ይህ ድርድር ከውሰት ውል መጠናቀቅ በኋላ በቋሚነት የመፈረም አንቀፅም ተካቶበታል። ከዝውውሩ በኋላ በአሰልጣኝ ሜልቪን ቦኤል ከ21 አመት በታች ቡድን ውስጥ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል ተብሎ የተገመተው ይህ ተስፈኛ  በውሰት ውሉ ደስተኛ እንደሆነ ገልጿል። “በጣም ጥሩ ስሜት ተሰምቶኛል። በአውሮፓ ትልቅ የወጣቶች አካዳሚ ውስጥ መጫወት ሁልጊዜም የማልመው ነገር ነበር። ዋናው አላማዬ በሚቀጥሉት ወራት በተቻለ መጠን ራሴን ማሳየት ነው” ብሏል።


የፌይኖርድ አካዳሚ ኃላፊ ሪኒ ኩለን በበኩላቸው “ከዚህ ቀደም ይስሐቅን ደጋግመን ተመልክተነዋል ፤ በታላቅ ፍላጎት ተከታትለነው ጥሩ እድገት እንዳለውም ዐይተናል። ተጫዋቹ በሚቀጥሉት ስድስት የውሰት ወራት ውስጥ የእግር ኳስ ሕይወቱን አንድ እርምጃ የማሳደግ ዕድሉ ይኖረዋል” ብለዋል።