ኢትዮጵያ መድን ከአጥቂው ጋር ተለያይቷል

ያለፉትን አምስት ወራት ከኢትዮጵያ መድን ጋር ቆይታ ያደረገው ናይጄሪያዊ አጥቂ ከቡድኑ ጋር መለያየቱ ታውቋል።

ስኬታማ ከነበረው የዓምና የውድድር ዘመን ጉዟቸው ማግስት ዘንድሮ ከአስራ ሦስት ጨዋታዎች በኃላ አስር ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ የተቀዛቀዘ ጅማሮ ያደረጉት ኢትዮጵያ መድኖች ከፊት መስመር አጥቂያቸው ቹኩዌመካ ጎድሰን ጋር በስምምነት መለያየቱ ታውቋል።

ያለፉትን አምስት ወራት ከቡድኑ ጋር ቆይታ የነበረው አጥቂው በሊጉ ተሳትፎ በማደረገባቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች በድምሩ ለ619 ደቂቃዎች ተሰልፎ መጫወት ሲችል በዚህም ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ቢችልም አሰልጣኙ በሚፈልጉት ደረጃ ውጤታማ ሊሆን ባለመቻሉ በሚል ከክለቡ ጋር በመነጋገር በስምምነት ለመለያየት መቻላቸውን እና ተጫዋቹ በአሁኑ ወቅት ወደ ሀገሩ እንዳቀና አውቀናል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን በደካማ ጉዞ ላይ የሚገኘውን ቡድናቸው ክፍተት ለማረም በቀጣይ የአጋማሹ የዝውውር መስኮት ሲከፈት በገበያው በንቃት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።