ሪፖርት | የቢኒያም ፍቅሩ የመጨረሻ ደቂቃ ግሩም ግብ የጦና ንቦቹ ከፈረሰኞቹ ነጥብ እንዲጋሩ አስችላለች

የሊጉ 111ኛ ጨዋታ 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ሲገናኙ ፈረሰኞቹ ፈረሰኞቹ በ13ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3ለ0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ አማኑኤል ኤርቦን አሳርፈው ዳግማዊ አርዓያን ሲተኩ የጦና ንቦቹ በተመሳሳይ ሳምንት ሀምበርቾን 1ለ0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ኢዮብ ተስፋዬን በማሳረፍ በብዙዓየሁ ሰይፉ ተክተዋል።


09፡00 ላይ በዋና ዳኛ ባሕሩ ተካ የፊሽካ ድምፅ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ዕረፍት የለሽ የሆነ እንቅስቃሴ ሲደረግ በኳስ ቁጥጥሩ ፈረሰኞቹ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም 4ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ በግራ መስመር ከማዕዘን አሻምቶት ፍሪምፖንግ ሜንሱ ሞክሮት የውጩ መረብ ላይ ካረፈው ኳስ ውጪ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች የጠሩ የግብ ዕድሎች በሁለቱም በኩል አልተፈጠሩም ነበር።

ጥሩ ፉክክር እያስተናገደ በቀጠለው ጨዋታ  20ኛው ደቂቃ ላይ ባየ ገዛኸኝ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሊጠቀምበት የሞከረውን ኳስ ተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ሲያጨናግፍበት በአራት ደቂቃዎች ልዩነት የጨዋታው የተሻለ የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ በጊዮርጊሶች አማካኝነት ተደርጓል። ዳግማዊ አርዓያ ከቢኒያም በላይ በተቀበለው ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በድንቅ ብቃት አስወጥቶበታል።

ከውሃ ዕረፍት በኋላ 29ኛው ደቂቃ ላይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ከሄኖክ አዱኛ ከቅጣት ምት በተሻገረለት ኳስ በግንባር ገጭቶ ካደረገው እና ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በቀላሉ ከያዘበት ኳስ በኋላ ድቻዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር መጫወት ችለው 34ኛው ደቂቃ ላይ ወሳኝ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። ቢኒያም ፍቅሩ ከአበባየሁ ሀጂሶ በተመቻቸለት ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት በመግባት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ይዞበታል።

በአጋማሹ የመጨረሻ አምስት ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች በቢኒያም ፍቅሩ አማካኝነት ሁለት የግብ ዕድሎችን አግኝተው አጥቂው 42ኛው ደቂቃ ላይ የተከላካዩን አማኑኤል ተርፉን ስህተት ተጠቅሞ ያደረገውን ሙከራ ራሱ ተከላካዩ ሲመልስበት ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አበባየሁ ሀጂሶ በግንባር ገጭቶ ባቀበለው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ይዞበታል።


ከዕረፍት መልስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ በተለይም በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ወላይታ ድቻዎች በአንጻሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ለመጫወት ፍላጎት ታይቶባቸዋል። ሆኖም ግን በአጋማሹ የመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለማየት አልቻልንም ነበር።

ጨዋታው 70ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ፈረሰኞቹ ጥረታቸው ሰምሮ ግብ አስቆጥረዋል። ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር በግራ እግሩ ያመቻቸለትን ኳስ የተቆጣጠረው ሞሰስ ኦዶ ከመሃል ተከላካዩ አንተነህ ጉግሳ ጋር ታግሎ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ወላይታ ድቻዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተሻለ ግለት የአቻነት ግብ ፍለጋ ቢታትሩም ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት ሲቸገሩ 80ኛው ደቂቃ ላይ ፍጹም ግርማ ከግራ መስመር አሻምቶት ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ከመለሰው በኋላ ኳሱን ያገኘው ብዙዓየሀ ሰይፉ ቢሞክረውም በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

86ኛው ደቂቃ ላይ ሀሰን ዘለቀ በዘላለም አባተ ተተክቶ በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ እንዲያገባ ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ 90+1ኛው ደቂቃ ላይ ድራማዊ ክስተት ፈጥረዋል። ቢኒያም ፍቅሩ ከረጅም ርቀት በአስደናቂ ሁኔታ የመታው ኳስ በግቡ የግራ ክፍል መረቡ ላይ አርፏል። ጨዋታውን የጨረሱ የሚመስሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በድጋሚ በመነሳሳት 90+6ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ቢኒያም በላይ ከግራ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ከጨረፈው በኋላ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ፍሪምፖንግ ክዋሜ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ እንደነበር እና በመጨረሻ ደቂቃዎች ትኩረት በማጣት በቀላል ስህተት ግብ ማስተናገዳቸውን ጠቁመው የማጥቃት ኃይላቸው ላይ በጉዳት ምክንያት በቂ አገልግሎት እንደሌለ ሲጠቁሙ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በበኩላቸው ፈታኝ እና ጠንካራ ጨዋታ እንደነበር ጠቅሰው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በቂ እንዳልነበር እና የግብ አጋጣሚዎችን ማምክናቸውን በመግለጽ ተቀይሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ የገባው ሀሰን ዘለቀ ለግቡ መገኘት ምክንያት እንደበር ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።