ሪፖርት | የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ ያለ ጎል ተቋጭቷል

ደካማ ፉክክር የተስተናገደበት የኢትዮጵያ መድን እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ መድን በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ካስተናገደበት ጨዋታው በአራቱ ተጫዋቾች ላይ ቅያሪን ሲያደርግ አዲሱ ተስፋዬ ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ አሚር ሙደሲር እና መስፍን ዋሼ ወጥተው አብዱልከሪም መሐመድ ፣ ያሬድ ካሳዬ ፣ ሰይድ ሐሰን እና ዮናስ ገረመው በምትኩ ወደ ሜዳ ሲገቡ በሀዋሳ በተመሳሳይ ተረተው የነበሩት ወልቂጤዎች በበኩላቸው ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ዳንኤል መቀጫን በወንድማገኝ ማዕረግ ፣ ተመስገን በጅሮንድን በመድን ተክሉ እንዲሁም መሳይ ፓውሎስን በራምኬል ሎክ ተክተዋቸዋል።

በውጤት ረሃብ ውስጥ ያሉ ክለቦችን ያገናኘው የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ ዝግ ያሉ እንቅሰቃሴዎች የበረከቱበት እና ጥራት ያላቸውን ሙከራዎች ለመመልከት ዕድለኞች ያልነበርንበት ነበር። መድኖች በተወሰነ መልኩ ወደ መስመር በማድላት በጥልቀት ለመጫወት አልፎ አልፎ ጥረት በሚያደርጉባቸው ጊዜያት የተቃራኒ ቡድን  ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ደርሰው የግብ ዕድልን በመፍጠሩ ረገድ ሻል ያለ መልክን ቢላበሱም የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው በእጅጉ ደካማ አቀራረብ ነበረው። ኳስን በሚይዙበት ወቅት መሐል ላይ ከሚደረጉ ንክኪዎች በኋላ ወደ ኮሪደር በመለጠጥ  ለመጫወት የሚዳዱት ወልቂጤዎች ጎል ለማስቆጠር የሚሄዱበት ርቀት እምብዛም ስኬታማ ሲያደርጋቸው አላስተዋልንም።

በተደጋጋሚ ወደ ቀኝ የሜዳው ክፍል በማድላት መድኖች በሚጫወቱበት ወቅት ጎል ለማስቆጠር የተወሰነ ፍላጎት ይታይባቸው እንጂ ወደ ግብነት ከመለወጥ አኳያ ድክመቶች ታይቶባቸዋል። 26ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መሐመድ በጥሩ ዕይታ ወደ ሳጥን የላከለትን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ በቀጥታ መቶ ዒላማዋን ሳትጠብቅ ኳሷ የወጣችበት አጋጣሚ ምንም እንኳን ጥራት አይኑራት እንጂ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ሆናለች። 27ኛው ደቂቃ ላይ በመሐመድ አበራ አማካኝነት መድኖች ጎል ቢያስቆጥሩም ሁለተኛ ረዳት ዳኛው ዘመኑ ሲሳዬነው በሚያወዛግብ መልኩ በእጅ ተነክቷል ካሉ በኋላ የፉክክር መንፈሱ እየወረደ ቀጥሎ 44ኛው ደቂቃ ላይ ወልቂጤዎች ከሳጥን ውጪ ሳምሶን ጥላሁን አክርሮ መቶ አቡበከር ኑራ በቀላሉ ከያዘበት ዕድል መልስ በይዘቱም ሆነ በሙከራም መድመቅ ያልቻለው ደካማው አጋማሽ ያለ ጎል ተጋምሷል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ ፉክክሩ ብዙም ሳይለወጥ የቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ተመልሰዋል። መድኖች ዮናስ ገረመውን በመስፍን ዋሼ ፣ ብሩክ ሙሉጌታን በያሬድ ዳርዛ ወልቂጤዎች በበኩላቸው ዳንኤል ደምሱን በሙሉዓለም መስፍን ተክተዋል። ወልቂጤ ከተማዎች በመጠነኛ መሻሻል ውስጥ ሆነው በሚያደርጉት የሽግግር ጨዋታ የጎል ዕድልን በአጋማሹ ጅማሬ ላይ ፈጥረዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ጋዲሳ ከቀኝ ወደ ውስጥ የሰጠውን ራምኬል ከግቡ ፊት ሆኖ ሊመታው ሲጥር በርናንድ ያስጣለው ኳስ ቡድኑን መሪ ሊያደርግ የሚችል ጥሩ አጋጣሚያቸው ነበረች።

በረጅሙ ወደ መስመር ኳስን በመጣል ያሬድ ዳርዛን ባማከለ መልኩ ወደ ፊት ተስበው ለመጫወት ይሞክሩ የነበሩት መድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ ወረድ ብለው መቅረባቸው በተለይ ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ የተጨማሪ ተጫዋችን ለውጥ ባደረጉት ወልቂጤ ከተማዎች ብልጫ ተወስዶባቸዋል። አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት መድን ተክሉ እና ራምኬል ሎክን በሔኖክ ኢሳያስ እና ዳንኤል መቅጫን ከተኩ በኋላ ቡድኑ የተጋጣሚ ሜዳ ላይ ቶሎ ቶሎ ተገኝቶ ዕድሎችን እንዲፈጥር አስችሏቸዋል። 60ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለን ኳስ የመድኑ ተከላካይ ሰይድ ሐሰን በግንባር ጨርፎ ወደ ኋላ የሰጠውን አቡበከር ሳኒ ከግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው ሳይቸገር ይዞበታል።

ወልቂጤ ከተማዎች የተሻለ መንቀሳቀሳቸውን በቀሪዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ቀጥለው በጋዲሳ የርቀት ሙከራ አድርገው 82ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግልፅ ዕድልን አምክነዋል። 83ኛው ደቂቃ ከርቀት ወደ ግራ ካደላ ቦታ የተገኘን የቅጣት ምት አዳነ በላይነህ ወደ ጎል በቀጥታ መቶ የግቡ አግዳሚ ብረትን ኳሷ ገጭታ ወጥታለች። ወልቂጤዎች የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ጎልን ለማስቆጠር በብርቱ መታገል ቢታይባቸውም ከፉክክር አኳያ ወረድ ያሉ አቀራረቦች የበዙበት ጨዋታ በመጨረሻም ያለ ጎል ፍፃሜውን አግኝቷል።


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የመድኑ አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ጨዋታው መጥፎም ጥሩም አይደለም ካሉ በኋላ በመከላከሉ ቡድናቸው ደካማ እንደሆነ እና በማጥቃቱም ካለን ችግር አንፃር ምንም ማድረግ አንችልም ሲሉ የተደመጡ ሲሆን በራስ መተማመኑን ቡድኑ ማጣቱንም ገልፀዋል። የወልቂጤ አቻቸው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በበኩላቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጋጣሚያቸው ብልጫ እንደነበረው ጠቁመው መረጋጋቶችም በቡድናቸው እንዳልነበር ከዕረፍት መልስ ግን ተነጋግረው ገብተው ጎል ለማስቆጠር በተሻለ መንቀሳቀስ መቻላቸውን አሰልጣኙ በንግግራቸው አውስተዋል።