ከወቅቱ የአዳማ ኮከብ ቦና ዓሊ ጋር የተደረገ ቆይታ

👉 “ሳላዲን ሰይድን በጣም ነው የምወደው ፤ አርዓያየ እሱ ነው።”

👉 “ለብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ሁሌም ነው የማስበው።”

👉 “በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ እንድጫወት ያደረገኝን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በጣም ነው የማመሰግነው።”

👉 “ቤተሰቦቼ እግርኳስ ተጫዋች እንድሆን ይደግፉኝ ነበር።”

ትውልድ እና ዕድገቱ ሻሸመኔ 010 ቀበሌ ውስጥ ሲሆን ለቤተሰቦቹም አራተኛ ልጅ ነው። ትልቅ እህቱ መካ ዓሊ እግርኳስ ተጫዋች ሆና ለሻሸመኔ ከተማ እና ለአምቦ አካዳሚ ተጫውታ በማሳለፏ በሷ ግፊትም ቤተሰቦቹ እርሱ ኳስ ተጫዋች እንዲሆን በጥሩ ሁኔታ ይደግፉት እንደነበር ያስታውሳል። ፎረስት በሚባል ሻሸመኔ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የጃማይካዎች ቡድን ውስጥ ጆርጅ በሚባል አሰልጣኝ ስር እግርኳስን ‘ሀ’ ብሎ መጫወት ጀምሯል። የሊዮኔል ሜሲን እንቅስቃሴ በመመልከት ገና በልጅነቱ በእግር ኳስ ፍቅር እንደተያዘ እና በትምህርቱ ጎበዝ የነበር ቢሆንም ከእግርኳስ ውጪ ምንም ሀሳብም ሆነ ፍላጎት እንዳልነበረው ይናገራል። ከፎረስት በኋላ ወደ አምቦ አካዳሚ ገብቶ ተጫውቷል። ራሱን እያሳደገ በመሄድም ለሻሸመኔ ከተማ አንድ ዓመት በተስፋ ተይዞ ከተጫወተ በኋላ በቀጣዩ ዓመት ወደ ዋናው ቡድን ተቀላቅሏል። በመቀጥልም በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አማካኝነት ለጅማ አባጅፋር ካለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ በአዳማ ከተማ ቆይታ እያደረገ ይገኛል። የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ቦና ዓሊ !

በዘንድሮው የአዳማ ከተማ ቆይታው በ511 ደቂቃዎች ሦስት ጎሎችን ማስቆጠር የቻለው እና ከዛም ባሻገር በተከታታይ ሳምንታት ሜዳ ላይ በሚያሳየው ታታሪነት እና የግል ክህሎት የብዙዎቹን ትኩረት የሳበው ቦና ዓሊ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

ከፕሪሚየር ሊጉ ጋር ትውውቅህ የጀመረው መቼ ነው ?

“2014 ዓ.ም ላይ ነበር። ለሻሸመኔ በግማሽ ዓመት 7 ጎሎችን አስቆጥሬ የወቅቱ የጅማ አባጅፋር አሰልጣኝ የነበረው አሸናፊ በቀለ ደወለልኝ እና ወደ ጅማ እንድሄድ ጠየቀኝ እኔም እርሱ ሲጠራኝ ደስ ብሎኝ ነበር ፤ ትልቅ አሰልጣኝ ነው። ብዙ የጨመረልኝ ነገር አለ ፤ ብዙ ለውጦኛል።”

የመጀመሪያ ጨዋታህን ከማን ጋር ምን ቦታ ላይ ተሰልፈህ ነበር ያደረግከው ?

“አዳማ ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር ተቃራኒ ሆኜ ነበር የተጫወትኩት። አሸናፊ እንደ አቅምህ ነው የሚያጫውትህ እና ለመጀመሪያ ጊዜ እንደፈረምኩ ቤስት ሆኜ ስገባ በጣም እመላለስ ስለነበር የመስመር ተከላካይ ሆኜ ነበር ፤ ከአንድ ጨዋታ በኋላ ግን ወደ ቦታየ ተመልሻለሁ።”

የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጎልህን ማን ላይ አስቆጠርክ ስሜቱስ እንዴት ነበር ?

“የመጀመሪያ ጎሌን አዳማ ከገባሁ በኋላ ዓምና በድሬዳዋ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ላይ ነበር ያስቆጠርኩት። ከጎል በጣም ርቄ ስለነበር በጣም ነው ደስ ያለኝ ማለት በአንዳንድ አጋጣሚዎች የውስጥ ችግር ምናምን ቢኖርም ብዙም ደስተኛ አልነበርኩም በጊዜው ማለት ጎል ሳገባ በሰዓቱ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር።”

በአሁኑ ሰዓት አዳማ ከተማ ከሜዳ ውጪ ባሉ ችግሮች እየታመሰ ቢሆንም የአንተ እንቅስቃሴ ላይ ያን ያህል ተጽዕኖ ያልፈጠረበት ምክንያት ምንድን ነው ?

“ምክንያቱ የውስጡ ችግር ብዙ ቢሆንም ለራስህ ብለህ ራስህን ለማውጣት መጫወት ስላለብህ ነው። ሲኒየሮቹ ቢኖሩ ብዙ እንጠቀም ነበር። እነሱ ባለመኖራቸው ትንሽ ጫና ፈጥሮብናል እላለሁ። ሆኖም አሸንፈናል ነገር ግን እንዲህ መቀጠል አንችልም። እኔ ደግሞ በራሴ አሪፍ የሆንኩት ከዚህ በኋላ ራሴን አሻሽየ እስከ ብሔራዊ ቡድንም ሆነ ከሀገር ውጪ መጫወት ስለምፈልግ አሁን ሥራዬ ላይ ነው ትኩረት ያደረግኩት ፤ አንዳንዴ በግል ዶርም ውስጥም ሆነ ጅምም እየሄድኩ እሠራለሁ።”

ከመስመር ስትነሳ ወይስ ከመሐል የቱን ትመርጣለህ ?

“ዘጠኝ ቁጥር ላይ ነው የምጫወተው ግን እንደ እኛ አጨዋወት አንዳንዴ መስመር ላይ ያለው ተጫዋች ወደ ውስጥ ሲገባ ወደ ውጪ ወጥተህ የምታጠቃበት ጊዜ ይኖራል ፤ ሁለቱም ቦታ ላይ አሪፍ ነኝ ብየ አስባለሁ ፤ አንዱ ወደ መስመር ሲወጣ አንዱ እየገባ ምናምን እንተጋገዛለን ለዛም ነው አሪፍ የሆነው ብየ አስባለሁ።”

ዘንድሮ በግልህ ምንድን ነው ያሻሻልከው ?

“በግል በመሥራቴ ጎል ላይ ያለኝን ነገር እያሻሻልኩ መጥቻለሁ። ጎል ላይ አሪፍ ሆኜ ነው የተገኘሁት ብየ አስባለሁ። አሰልጣኙ ከሚሰጠን ትሬኒንግ በተጨማሪ በግል በመሥራቴም ነው።”

ሀገር ውስጥ አርዓያህ ማን ነው ?

“ሳላዲን ሰይድን በጣም ነው የምወደው ፤ አርዓያየ እሱ ነው።”

ስለ ብሔራዊ ቡድን ማሰብ ጀምረሃል ?

“አዎ ሁሌም ነው የማስበው። እጫወታለሁ ብየም አስባለሁ። ብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ዕድሜ ላይ ችግር ያለ አይመስለኝም። ባሳየኸው ነገር ነው የምትመረጠው እና በማሳየው ነገር እንዲጠሩኝ እፈልጋለሁ። ብሔራዊ ቡድኑን ማገልገል እፈልጋለሁ።”

ከአዳማ ከተማ ጋር ምን ታስባለህ ?

“በዚህ ዓመት ውል ጨራሽ እንደመሆኔ ያው ብንችል ቻምፒዮን ብንሆን ደስ ይለኛል ካልሆነም ከአንድ እስከ ሦስት ይዘን ብንወጣ ደስ ይለኛል። ደግሞም እናደርገዋለን ብየ አስባለሁ።”

በዚህ ብቃትህ እየጨመርክ እንዳትሄድ ሊያደርግህ የሚችል ምክንያት ይኖራል ?

“በዚህ እንዳልቀጥል ምንም የሚመጣብኝ ጫና የለም። አሁን ያለሁበትን ቴምፖ እና አቅም ሙሉ  ለሙሉ ይዤ እጨርሳለሁ ብየ አስባለሁ።”

በእግርኳሱ እዚህ ለመድረስህ የምታመሰግናቸው አካላት ካሉ…

“ከፈጣሪ በታች ዋነኞቹ ቤተሰቦቼ ናቸው። ከዛም በመቀጠል በመጀመሪያ ፎረስት ነበር የተጫወትኩት እና የዛ ቡድን አሰልጣኝ ጆርጅ የሚባል እንግሊዛዊ ነበር። ከእርሱ በመቀጠል ዴሻ የሚባል አሰልጣኝም አለ ሌላም ደግሞ ፕሪሚየር ሊጉ ላይ እንድጫወት ዕድል የሰጠኝን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን በጣም ነው የማመሰግነው።”