በዱባይ የሚደረገውን የሸገር ደርቢ ጨዋታ አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ

👉”ወደ ድሬዳዋ ተሰደን ተጫውተናል ፤ ወደ አዳማ ተሰደን ተጫውተናል ፤ እስቲ በደንብ እንሰደድ ብለን ወደ ዱባይ ተሰደን እንጫወታለን…” አቶ ገዛኸኝ

👉”አንጋፋ ደጋፊዎቻችንን የምናገኝበት እንዲሁም አዳዲስ ደጋፊዎችን የምናፈራበት ጉዞ ነው” አቶ ሰለሞን

👉”የኢትዮጵያ ክለቦች ዓለም አቀፍ ልምድ እንዲያገኙ ነው ጉዞው የተዘጋጀው” አቶ ፍፁም

የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የሆነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር የመጀመሪያውን ዙር ፍልሚያ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ የሚያጠናቅቅ ሲሆን የሁለተኛው ዙር ውድድር ከመጀመሩ በፊትም ሁለቱ የሀገራችን ክለቦች ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱባይ አምርተው የሸገር ደርቢ ጨዋታቸውን እንደሚያከናውኑ ይጠበቃል። ይህንን ለአምስት ቀናት የሚቆይ የጉብኝት ጨዋታን በተመለከተም በዛሬው ዕለት የጉዞ አዘጋጁ፣ የክለቦቹ ተወካዮች እንዲሁም የጉዞ ስፖንሰሮች አመራሮች ተገኝተው ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የሁለቱን ክለቦች የዱባይ ጨዋታ ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ብቸኛ የፊፋ የጨዋታዎች ኤጀንት አቶ ፍፁም አድነው “የኢትዮጵያ ክለቦች ዓለም አቀፍ ልምድ እንዲያገኙ ነው ጉዞው የተዘጋጀው” በሚል በጀመረው ማብራሪያው ይህ የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞ የመጀመሪያ እንደሆነና ሁለቱ ክለቦች የተመረጡት ባላቸው ተቀባይነት፣ ውጤታማነት እና የደጋፊ ብዘት እንደሆነ ጠቁሞ በቀጣይም በሊጉ የዕረፍት ጊዜያት ከሌሎች ክለቦች ጋር መሰል ስራዎችን እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

አቶ ፍፁም በገለፃቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የካቲት 15 ምሽት 4 ሰዓት ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ ጉዞዋቸውን እንደሚጀምሩ ተናግረው ለሊት 11 ሰዓት ዱባይ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው ወደተዘጋጀላቸው ማረፊያ አምርተው ምሽት ላይ የእራት ግብዧ ፕሮግራም እንደሚካሄድ አውስተዋል። በዚህ የእራት ግብዧ ፕሮግራም ላይ ለሁለቱም ክለቦች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር እንደሚዘገጅና በጨረታ በሚቀርቡ ቁሳቁሶች ለክለቦቹ ገቢ ለመሰብሰብ እንደታቀደ ተመላክቷል።

በማግስቱ በዱባይ የጉብኝት መርሐ-ግብር ተከናውኖ በቦለርስ አካዳሚ ቡድኖቹ ልምምድ እንደሚሰሩ በዛው ሰዓት የክለቦቹ አመራሮች ደግሞ ቦለርስ አካዳሚ በሚያዘጋጀው ሚኒ ሴሚናር ላይ ተሳትፈው የአካዳሚዎቻቸውን ግንባታ እና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ውይይት በማድረግ የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ሥነ-ስርዓት እንደሚከናወን ተመላክቷል። የካቲት 17 ደግሞ የሸገር ደርቢ ጨዋታ እንደሚከናወን ተብራርቷል።

በመቀጠል መድረኩን የተረከቡት የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥራ-አስኪያጀረ አቶ ሰለሞን በቀለ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና ሥራ-አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ጉዞውን ላዘጋጀው አካል ምስጋና አቅርበው በዱባይ ቆይታቸው ከሚያደረጉት የሸገር ደርቢ ጨዋታ ውጪ በርቀት ያሉ ደጋፊዎቻቸውን የሚያገኙበት አጋጣሚ ስለሆነ የተለያዩ መርቸብዳይዞችን በመሸት ገቢ ለማግኘት እንዳሰቡ ተናግረዋል። በተለይ አቶ ገዛኸኝ ያለፉትን ዓመታት የሸገር ደርቢ ጨዋታ በመዲናችን አለመደረጉን ጠቅሰው “ወደ ድሬዳዋ ተሰደን ተጫውተናል ፤ ወደ አዳማ ተሰደን ተሰደን ተጫውተናል ፤ እስቲ በደንብ እንሰደድ ብለን ወደ ዱባይ ተሰደን እንጫወታለን።” ያሉት አባባል በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አካላትን ፈገግታ ያስጫረ ነበር።

በስፍራው የሚደረገው ጨዋታው የፊፋን መስፈርት እንዲያሟላ የኢንሹራንስ ጉዳይ መጠናቀቁን እንዲሁም አጠቃላይ ሁነቶችን ሀገር ውስጥ ለሚገኙ አካላት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ለማስተላለፍ ከባላገሩ ቴሌቭዥን ጋር ስምምነት መፈፀሙ የተገለፀ ሲሆን የስታዲየም መግቢያ ዋጋም በአንድ አጋር አማካኝነት ከ60 እስከ 120 ድራም ድረስ እንደሚሸጥ ተብራርቷል።

በመጨረሻም ወደ ስፍራው ከቡድኖቹ ጋር ማምራት ለሚፈልጉ ሰዎች ልዩ ፓኬጅ እንደተዘጋጀ የተናገሩት አዘጋጁ አቶ ፍፁም አቅም የሌላቸው ደጋፊዎችንም ከክለቦቹ ጋር ተነጋግረው በነፃ እንደሚወስዱ አመላክተዋል።