የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ14ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሥራ አራተኛ ሳምንት ጎልተው በወጡ ተጫዋቾች ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አደራደር ፡ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ሰዒድ ሀብታሙ – አዳማ ከተማ

አዳማ ከተማ ፋሲል ከነማን ገጥሞ 1ለ1 ባጠናቀቀበት ጨዋታ ቡድኑ አንድ ነጥብን ይዞ ከሜዳ እንዲወጣ የግቡን በር በንቃት የጠበቀው ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ የነበረው ሚና ቀላል አልነበረም። ፋሲሎች በቅብብል ሂደትም  ሆነ ከርቀት ያደርጓቸው የነበሩ ኳሶችን ይመክትበት ከነበረበት አስደናቂ ብቃት አኳያ በሳምንቱ የምርጥ ስብስባችን አካል ሆኗል።

ተከላካዮች

ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ጊዮርጊሶች በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ ከወላይታ ድቻ ጋር 1ለ1 ሲለያዩ የመስመር ተከላካዩ እንቅስቃሴ እጅግ ግሩም ነበር። ባልተገደበ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተጋጣሚን የግብ ክልል በተደጋጋሚ መፈተን የቻለው ሄኖክ ሞሰስ ኦዶ ላስቆጠራት የቡድኑ ብቸኛ ግብም አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

አስጨናቂ ጸጋዬ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሀድያ ሆሳዕና ወርቃማ ሦስት ነጥብን ከባህር ዳር ላይ ሲወስድ የመከላከል ሂደቱን በአግባቡ ካሳለጡ ተጫዋቾች መካከል አስጨናቂ ከፍ ያለውን ድርሻ ይወስዳል። የሚሻገሩ የዓየር ላይ ኳሷችን በማቋረጥም ሆነ በተለይ በአንድ አጋጣሚ ሀብታሙ ታደሠ ለማስቆጠር ከግቡ ትይዩ ሆኖ ያገኘውን መልካም አጋጣሚ ያከሸፈበት መንገድ አግራሞት የሚያጭር ነበር።

ወንድሜነህ ደረጄ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን በሊጉ መሪ መቻል ላይ በጎል ደምቆ ባስመዘገበበት ሳምንት የመሐል ተከላካዩ ወንድሜነህ የመቻል የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች የግብ ዕድል የሚፈጥሩበትን ክፍት ቦታ በመቆጣጠር ቦታውን አስከብሮ ቡድኑ ውጤት ይዞ እንዲወጣ ያበረከተው አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ነበር።

በፍቃዱ ዓለማየሁ – ኢትዮጵያ ቡና

ከጨዋታ ጨዋታ ይበልጥ እየበሰለ የመጣው ወጣቱ የመስመር ተከላካይ በያዝነው ሳምንትም ሜዳ ላይ ጥሩ ሆኖ ውሏል። የመቻልን የመስመር ማጥቃት በተለይም ደግሞ በቀኝ ቦታ ተሰልፎ የነበረውን የከነዓን ማርክነህን እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ በማክሸፍ ለቡድኑ ውጤታማነት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

አማካዮች

በዛብህ መለዮ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡናዎች ከመመራት ተነስተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2ለ1 በረቱበት መርሐግብራቸው በመጀመሪያው አጋማሽ 33ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑ እየተመራ ተቀይሮ የገባው በዛብህ መለዮ ወደ ሜዳ ከገባ በኋላ የቡድኑን የማጥቃት ሚዛን ከመጠበቅ ባለፈ 44ኛው ደቂቃ ላይ ወሳኟን የአቻነት ግብ በግሩም ክህሎት አስቆጥሮ ቡድኑ በይበልጥ ወደ ጨዋታ ገብቶ ድልን እንዲያሳካ ያደረገው ጥረት ከፍ ያለ ነበር።

አዲሱ አቱላ – ሀዋሳ ከተማ

በሀዋሳ ከተማ ቡድን ውስጥ በመጨረሻዎቹ ተከታታይ ጨዋታዎች በቋሚ አሰላለፍ በመግባት ታታሪነቱን እያሳየ የሚገኘው አዲሱ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ሀምበርቾን 2ለ0 ሲረታ መሃል ሜዳው ላይ ለወሰዱት ብልጫ ዋና ምክንያት የነበር ሲሆን ከሳጥን ውጪ ግሩም ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦም በግቡ የቀኝ ቋሚ ተመልሶበታል።

አብዱልከሪም ወርቁ – ኢትዮጵያ ቡና

ቡናማዎቹ የሊጉን መሪ መቻልን ረምርመው 4ለ0 ሲያሸንፉ እጅግ ስኬታማ ቀን ያሳለፈው አብዱልከሪም መስፍታ ታፈሰ እና መሐመድኑር ናስር ላስቆጠሯቸው ግቦች አመቻችቶ ማቀበል ሲችል አንድ ግብም በራሱ ስም ማስመዝገብ በመቻሉ ያለ ተቀናቃኝ በቦታው ተመራጭ ሆኗል።

አጥቂዎች

ቢኒያም ፍቅሩ – ወላይታ ድቻ

የጦና ንቦቹ ከፈረሰኞቹ ጋር 1ለ1 በተለያዩበት ጨዋታ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ የግብ ዕድሎችን የፈጠረው ቢኒያም ቡድኑ ሊሸነፍ በተቃረበበት ሰዓትም ከረጅም ርቀት በውድድሩ ከታዩ ድንቅ ጎሎች መካከል አንዱን ማስቆጠር ችሏል።

ዓሊ ሱሌይማን – ሀዋሳ ከተማ

ኤርትራዊው የኃይቆቹ ፈጣን አጥቂ ቡድኑ ሀምበርቾን 2ለ0 ሲረታ እጅግ በርካታ የሆኑ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ከመቻሉ ባሻገር የቡድኑን የመጀመሪያ ግብ ከሳጥን ውጪ ማስቆጠር ሲችል ለተባረክ ሄፋሞ ግብም አመቻችቶ ማቀበል መቻሉ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ አድርጎታል።

ቦና ዓሊ – አዳማ ከተማ

ከሜዳ ውጪ ባሉ ተግዳሮቶች እየተፈተኑ የሚገኙት አዳማዎች ከፋሲል ከነማ ጋር 1ለ1 ሲለያዩ የቦና ብቃት የሚደነቅ ነበር። አጥቂው 72ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ለመውጣት ቢገደድም በቆየባቸው ደቂቃዎች ካደረገው ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ባሻገር ለተመልካች ሳቢ የሆኑ ክህሎቶችን ሲያሳይ የቡድኑን ብቸኛ ግብም አስቆጥሯል።

አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ – ኢትዮጵያ ቡና

ቡናማዎቹ የሊጉ መሪ መቻል ላይ የጎል ዝናብ አውርደው 4ለ0 ሲያሸንፉ አሰልጣኙ ለጨዋታው ይዘው የቀረቡት አጨዋወት እጅግ የሚደነቅ ነበር። በተለይም በተቃራኒ ቡድን በኩል የግብ ዕድል ፈጣሪ የሆኑ ተጫዋቾችን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ እና በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ለመጫወት መርጦ የገባው ቡድን ለተመልካች እጅግ ሳቢ የነበር ከመሆኑ ባሻገር ግብ ሳያስተናግድ መውጣቱን ምክንያት በማድረግ አሰልጣኝ ነጻነት ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር ተፎካክረው የሳምንቱን ምርጥ ቡድናችንን እንዲመሩ ተመርጠዋል።

ተጠባባቂዎች

ታፔ አልዛየር – ሀዲያ ሆሳዕና
አዳነ በላይነህ – ወልቂጤ ከተማ
አናጋው ባደግ – ወላይታ ድቻ
መስዑድ መሐመድ – አዳማ ከተማ
መለሰ ሚሻሞ – ሀዲያ ሆሳዕና
አማኑኤል አድማሱ – ኢትዮጵያ ቡና
ዳዋ ሆቴሳ – ሀዲያ ሆሳዕና
አለን ካይዋ – ሻሸመኔ ከተማ