ማቲያስ ምትኩ አዲስ ክለብ አግኝቷል

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የመስመር ተጫዋች ወደ ሶለንቱና አቅንቷል።

በእናት ክለቡ ዱርጋርደን ባሳየው እንቅስቃሴ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ትውልደ ኢትዮጵያዊው የ22 ዓመት የመስመር ተጫዋች ማቲያስ ምትኩ በስዊድን ታችኛው ዲቪዝዮን ለሚሳተፈው ሶለንቱና ፈርሟል።


በመጀመርያዎቹ የእግር ኳስ ሕይወቱ ዓመታት ላይ ትልቅ ተስፋ ከሚጣልባቸው ባለ ተሰጥዖ ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ይህ ተጫዋች የእግር ኳስ ሕይወቱ በሚጠበቀው ደረጃ መቀጠል አልቻለም። ክለቡ ዱርጋርደን ከወቅቱ ሻምፒዮን ማልሞ ጋር ባደረገው ጨዋታ በእግር ኳስ ሕይወቱ የመጀመርያው ጨዋታ ባደረገበት ዕለት ክለቡ ከሁለት ለባዶ መመራት ተነስቶ ጨዋታውን እንዲያሸንፍ ያስቻሉ ግቦች ካስቆጠረ በኋላ የበርካቶች ትኩረት ስቦ የነበረው ይህ ተጫዋች ባለፉት ዓመታት ለ Eskilstuna፣ IF Karlstad፣ IFk Haninge ለተባሉ ክለቦች ሲጫወት ከቆየ በኋላ ለሶለንቱና መፈረሙ ክለቡ በይፋዊ ድረ ገጹ አስታውቋል።


ፊርማውን አስመልክተው ከክለቡ ይፋዊ ድረ ገጽ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክለቡ የስፖርት ዳይሬክተር ፖጃ ናዴራ ተጫዋቹን በማስፈረማችን በጣም ደስተኞች ነን ካሉ በኋላ የክለቡን ውጤት ይበልጥ የተሻለ ለማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል። የክንፍ ተጫዋቹ ከEskilstuna ጋር በቆየበት ያሳለፍነው የውድድር ዘመን በአሥራ ሁለት ጨዋታዎች ተሰልፎ ተጫውቷል።